በዳውሮ ዞን የማና ጎሳ አባላት ላይ የተፈጸመ አሳዛኝ ጥቃት እና ማህበራዊ መገለል እንዲቆም ተጠየቀ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን፣ ማሪ ማንሳ ወረዳ፣ ሴሪ ቀበሌ የሚኖሩ የማና ጎሳ አባላት ላይ አሳዛኝ ጥቃት መፈጸሙን ለ WT Media ገልጸዋል።
የማህበረሰቡ አባላት እንደተናገሩት፣ በየጊዜው በሚደርስባቸው ማህበራዊ መገለልና አካላዊ ጥቃት ምክንያት ሕይወታቸው ስጋት ላይ ወድቋል።

በሸክላ ስራ ተሰማርተው የሚተዳደሩት የማና ጎሳ አባላት፣ በማንነታቸው ምክንያት ከሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ከፍተኛ መገለል እንደሚደርስባቸው አስረድተዋል።
ከዚህም ባሻገር ከትምህርት፣ ከጤና እና ከሌሎች መሰረታዊ ማህበራዊ አገልግሎቶች ጭምር ተገልለው እንደሚኖሩ ተናግረዋል።
የጎሳው አባላት እንዳሉት፣ ባልተፃፈ ህግ ምክንያት ለዘመናት በፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ተሳትፎዎች ላይ እንዳይሳተፉ ተከልክለዋል።
ሁኔታውን ሲገልፁም፣ “እንደ ሰው ሳይሆን እንደ እንስሳ ተቆጥረው በመገለል እንደሚኖሩ” በቁጭት ተናግረዋል።
የጎሳው አባላት በቅርቡ በአካባቢው ማህበረሰብ ጥቃት እንደደረሰባቸው በመግለፅ፣ የመኖሪያ ቤታቸው ከንብረት ጋር ሙሉ በሙሉ በእሳት እንዲቃጠል መደረጉን ለWT Media አስታውቀዋል።


ከዚህም የከፋ የሚያደርገው፣ በማህበረሰቡ ውስጥ የማና ጎሳ አባልን ስለገደለ ወይም ቤቱንና ንብረቱን ስላቃጠለ “በህግ አይጠየቅም” የሚል አመለካከት በስፋት መኖሩን አስረድተዋል።
“በአከባቢው ያለው ህግና የህግ ሰዎችም እኛን እንደ ሰው አያዩም” ሲሉ አሳዛኝ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
የማና ጎሳ አባላት በስራቸው የሚያመርቱትን ሸክላ እና ግብርና ምርቶች ሌሎች ማህበረሰቦች እየተጠቀሙ፣ በጎሳው አባላት ላይ ግን ሁልጊዜ ጥቃት መፈጸሙ “ኃጢአት” ነው ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
የእነሱ ድምፅ ለዘመናት ታፍኖ መቆየቱን በመግለፅ፣ “የሚመለከተው አካል እኛን ከዚህ አሰከፊ ጥቃትና መገለል ሊያወጣ ይገባል” ሲሉ ለመንግስት እና ለሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ተማፅኖ አቅርበዋል።
WT Media በጉዳዩ ዙሪያ ከዳውሮ ዞን የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ማብራሪያ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም፣ ለጊዜው ምላሽ ማግኘት አልተቻለም።
ማሳሰቢያ፦ WT MEDIA በሀገሪቱ በተለይም ደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት በማያገኙ ለተጮቆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው እውነትንና ሀቅን መሠረት አድርገው የሚሰራ ስለሆነ የመረጃ ሰጪ ግለሰቦች ምስጥርና ደህንነት በተጠበቀ ሁኔታ የደረሱን መረጃዎችን መልሰን አጣርተን ለህዝብና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት በታማኝነት ይፋ እናደርጋለን።
ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ፋይዳ ባላቸው ህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳባችሁን ለማካፈል ለሚፈልጉ ሁሉ ዘውትር በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነን እውነት፣ ሀቅ፣ ፍትህ፣ ግልፅነት፣ ሰብዓዊነት፣ ቅንነትና ሚዛናዊነት የሚፀባረቅበት በሌሎች ትላልቅ ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለ ዘውትር አብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው!! እኛ ዘውትር የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን !!
Voice of Marginalized Community – WT Media