IMG_20251126_220419_052

#ሰበርመረጃ

በጎፋ የመሬት መንሸራተት እርዳታ ከተሰበሰበው ላይ 60+ ሚሊዮን ብር ለማጭበርበር ሲል የተያዘው ግለሰብ “ከፍተኛ አመራሮች 5 ሚሊዮን ብር ኮምሽን ለመስጠት ቃል ስለገቡ ነው” የሚል ቃል ለፍርድቤት መስጠቱ ተገልጿል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች ከተሰበሰበው ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ከሆነው የእርዳታ ገንዘብ ስርቆት ጋር በተያያዘ፣ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር።

WT Media ዛሬ ፍርድ ቤት ውሎውን ተከታትሎ እንዳረጋገጠው፡

1. የምርመራ ጊዜ መራዘም እና የተለቀቀች ተጠርጣሪ

ዛሬ በፍርድ ቤቱ ፊት የቀረቡት 3 ወንዶች እና 4 ሴቶች በድምሩ 7 ተጠርጣሪዎች ናቸው።

በፍርድ ቤቱ ውሎ ከአንዷ ሴት ተጠርጣሪ ውጪ፣ በቀሪዎቹ ላይ ለተጨማሪ ምርመራ 11 ቀናት ተፈቅዷል። 1ኛዋ ሴት ተጠርጣሪ በዋስ ተለቅቃለች።

2. ተጠርጣሪው መሐመድ ኑሩሁሴን ስራጅ የሰጠው ቃል

WT Media በፍርድ ቤት ውሎ ላይ ከተገኘ ምንጭ እና ጉዳዩን በቅርበት ከሚከታተሉ አካላት ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ተጠርጣሪው አቶ መሐመድ ኑሩሁሴን ስራጅ ለፍርድ ቤት ባቀረበው ቃል በቃል ጥያቄ የጉዳዩን አቅጣጫ የሚያሳይ ከባድ ክስ አቅርቧል፡

“ይህን ገንዘብ ለማዛወር በግለሰቦች ተጠርቼ ለ5 ሚሊዮን ኮሚሽን ነው የገባሁት። ነገር ግን ይሄን ያስተባበሩ ባለሥልጣናት፣ ባለሃብቶችና ባለሙያዎች ስማቸውን፣ ስልካቸውንና ፎቶቸውን ጨምሮ ከዞን እስከ ክልል ያለውን ሰጥቻለሁ” ብሏል።

አክሎም “ነገር ግን መርማሪ ፖሊስም ሆነ አቃቤ ሕግ እነዚህን መያዝና ማቅረብ አልቻለም። እኔ በግሌ ጠያቂ በሌለበት እየተሰቃየሁ ነኝ” የሚለውን ለፍርድ ቤት አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱ በዚህ ከባድ ክስ ላይ ምንም ተጨባጭ ምላሽ አልሰጠም፣ ይህም ምርመራው “ታፍኗል” የሚል ስጋት እንዲፈጠር አድርጓል።

3. ከሀገር የሸሹት ባለሥልጣናት

በጉዳዩ ላይ ጠንከር ያለ መረጃ ያላቸው ሁለት ቁልፍ ባለሥልጣናት ከሀገር ሸሽተው በስልጠና ስም ቻይና መግባታቸው ተገልጿል።

1ኛ የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ደግፈ፣ የክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አቶ ጋንታ ጋምአ ናቸው።

ይህ ከሀገር መሸሽ የ60+ ሚሊዮን ብር የእርዳታ ገንዘብ ስርቆት ቅሌት ከክልል እስከ ዞን ያሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን የሚያካትት ሰፊ የመዋቅር ወንጀል መሆኑን የሚያመላክት ነው ተብሏል።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media