1000084706

በዎላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ባለው የረጅም ጊዜ የህብረተሰቡ ጥያቄ የነበረው የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ዙሪያ፣ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዎላይታ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መላከ ሰላም ቀሲስ ቦክቻ እንጋ እና በፖለቲካ ተንታኝና ምሁር ረ/ፕሮፌሰር አሰፋ ወዳጆ መካከል ከፍተኛ የሐሳብ ግጭት ተፈጥሯል።

WT Media የተመለከተው ሁለቱም ወገኖች የኦቶና ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ደብር ይዞታ መነካካትን አስመልክቶ የራሳቸውን አቋም ያቀረቡ ሲሆን፣ ውይይቱ ከልማት ጥያቄ አልፎ ወደ ሃይማኖት-ብሔር ተኮር ክርክር ተሸጋግሯል።

ቀሲስ ቦክቻ እንጋ የመንገድ ልማቱ የቤተ ክርስቲያኗን ሕጋዊ ይዞታ በመጣስ ከ400 በላይ አፅመ ሙታን ያረፈበትን መካነ መቃብር ለማንሳት መታቀዱን በመቃወም ሀሳብ አቅርበዋል።

የመንገዱ ዲዛይን “የግለሰብ ይዞታ እንዳይነካ ተብሎ” ሆን ብሎ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይዞታ እንዲገባ የተደረገ አሠራር መሆኑን ገልጸው፣ ይህንን ሙከራ “ጸረ-ኢኦተቤክ ፖለቲካ ሴራ” እና በምድረ ዎላይታ ቤተ ክርስቲያንን “ባይተዋር የማድረግ ሙከራ” ሲሉ ወንጅለዋል።

ቤተ ክርስቲያኗ የሠራቻቸው ላሜራ ሱቆች ከይዞታ ውጭ ናቸው የሚለው ወሬ ትክክል እንዳልሆነ በመግለጽ፣ “ላሜራው ሲነካ መቃብሩም ይነካል” የሚል አቋም ይዘዋል።

ረ/ፕሮፌሰር አሰፋ ወዳጆ በበኩላቸው፣ ቀሲስ ቦክቻ ኤንጋ የሚያራግቡት ፕሮፓጋንዳ “ውሃ የማይቋጥር እና በተጨባጭ ማስረጃ ያልተደገፈ” መሆኑን በመግለጽ፣ ጉዳዩን ወደ ብሔር ማዞሩን ክፉኛ ተችተዋል።

ፕሮፌሰሩ፣ ይህ የቄስ ቦክቻ አገላለጽ “አደገኛ መዘዝ ያረገዘ (ሃይማኖት-ብሔር ተኮር ጥርጣሬ፣ ጥላቻና ግጭት ሊያስከትል የሚችል) የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ” እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የዎላይታ ሕዝብ የቤተ ክርስቲያኗ ጠባቂ መሆኑን በመረጃ በማስደገፍ፣ ኢትዮጵያ በፋሺስት ኢጣሊያ ስትወረር እንኳን ቤተ ክርስቲያንን አክብራ የጠበቀች ብቸኛ ምድር ዎላይታ መሆኑን አስታውሰዋል።

በመሆኑም፣ “ዎላይታን የኢኦተቤክ ጠል አድርጎ ማቅረብ” ተቀባይነት የለውም ሲሉ ይሞግታሉ።

የይዞታ እና የካሳ ጥያቄዎች ካሉ፣ የደብሩ ኃላፊዎች ከከተማ አስተዳደሩ እና ከሌሎች መንግሥታዊ አካላት ጋር ተወያይተው “win-win” መፍትሔ ማግኘት እንደሚችሉ አስቀምጠው፣ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን የሚያሰራጩ ሁሉ “አደብ እንዲገዙ” አሳስበዋል።

ይህ ክርክር በዎላይታ ሶዶ ላይ ባለው የልማት ፕሮጀክት ዙሪያ ፍትሃዊ ካሳ እና የሕግ አሠራር ላይ መታየት ሲገባው፣ ቀሲስ ቦክቻ ኤንጋ በግል ክስተቶች (እንደ ሞባይል ስርቆት) ወቅት ሳይቀር ጉዳዩን ወደ ብሔርና ፖለቲካዊ ሴራ የማምጣት ዝንባሌያቸው በአካባቢው ምሁራንና ሕዝብ ዘንድ አሳሳቢ ሆኗል።

ከዘጠኝ ወር በፊት ቀሲስ ቦክቻ እንጋ በግል የፌስቡክ ገጻቸው አማካኝነት ባልተለመደ ሁኔታ “ከነቤተሰቦቼ ለመሰደድ ዝግጁ ነኝ… በልጆቼ ላይ በተጠና ሁኔታ ተከታትለው የተፈጸመው የግድያ ሙከራና የስልክ ዘረፋ በእጅጉ አሳዝኖኛል” በማለት፣ የግል የወንጀል ክስተትን “በኢትዮጵያዊ ስሜት እንጂ በእናንተ አስተሳሰብ ለእኔም ሀገር አለኝ” በሚል አገላለጽ ከብሔር ጋር የሚያያዝ መልዕክት አስፍረው ነበር።

ይህ መልእክት በኦርቶዶክስ ምዕመናን እና በዎላይታ ተወላጆች ዘንድ “ድርጊቱ የግለሰብ የወንጀል ክስተት እንጂ የዎላይታ ሕዝብ ዘር ቆጥሮ የፈጸመው ጥቃት አይደለም፣ ለ29 ዓመታት ሲኖሩ ያላስታወሱትን የማንነት ፍለጋ መዳከር ተገቢ አይደለም” በማለት፣ ዎላይታ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የዋለችውን ውለታና ያለውን ታሪካዊ ክብር የነካ ነው” በሚል ገልፀው ነበር።

በሕዝቡና በምዕመናን ከፍተኛ ግፊት፣ ቀሲስ ቦክቻ ኤንጋ በሚቀጥለው ቀን “በጥቂት ግለሰቦች ምክንያት ብዙኃኑን የነካ ስለሆነ ይቅርታ እንድጠይቅ በመከሩኝ ምክር መሠረት ቅር የተሰኛሁ ሁሉ በእግዚአብሔር ስም ይቅርታ እንድታደርጉልኝ እጠይቃለሁ” በማለት በግልፅ ይቅርታ ጠይቀው ነበር።

በአጠቃላይ፣ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሥራ አስኪያጅ የአቋም መግለጫዎች፣ ከግል ወንጀል እስከ የከተማ ልማት ጉዳዮች ድረስ ከብሔርና ከፖለቲካ ጋር እየተያያዙ መቅረባቸው በዎላይታ ሕዝብ እና በእምነት ተቋማት መካከል መቻቻልና ሰላም ያለበትን ግንኙነት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል የሚል ስጋት እየፈጠረ ይገኛል።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media