የፌዴራል ጭማሪ ለሁሉም ሲለቀቅ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የወረዳ ሠራተኞችን የመስከረም ውዝፍ ደመወዝ ከልክሎ ለአመራር ስልጠና “ለካድሬ ዓላማ” ሊያውለው ነው መባሉ በሰራተኞች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ መፍጠሩ ተገልጿል።
የፌዴራል መንግሥት ለሁሉም የመንግሥት ሠራተኛ ያደረገው የደመወዝ ጭማሪ ማሻሻያ ገንዘብ “ያለ ምንም እንከን” ወደ ክልሎች የተለቀቀ ቢሆንም፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአመራር ደረጃ የተሰጠ የተሳሳተ አቅጣጫ ምክንያት በመስጠት የወረዳ መዋቅር የመንግሥት ሠራተኞች የመስከረም ወር ጭማሪ ደመወዝ ተከልክለዋል።
WT Media ከተለያዩ ምንጮች ባገኘው መረጃ መሠረት፣ ይህ የደመወዝ ረገጣ “ለካድሬ ስልጠና” የሚሆን በጀት ለማሰባሰብ ያለመ እንደሆነ ተጠቁሟል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመስከረም ወር 2018 ዓ.ም. የደመወዝ ጭማሪን በመዝለል፣ የጥቅምት ወር ደመወዝን ብቻ ከፍሏል።
የመስከረም ወር ውዝፍ ደመወዝ የተከፈለው ለክልል ብሮዎች፣ ለዞን መምሪያዎች እና ለከተማ አስተዳደሮች ብቻ ነው።
ሰራተኞቹ “ዋና ሥራ ያለውና ደፋ ቀና የምለውን” የወረዳ መዋቅር የመንግሥት ሠራተኛን ክፍያ ሙሉ በሙሉ ተከልክሏል የሚል ቅሬታ አሰምተዋል።
ይህ የመስከረም ወር ክፍያ ለወረዳ መዋቅሮች እስከ ዛሬ ድረስ ያልተከፈለበት ዝርዝር ይፋ የሆነ ምክንያት ባይኖርም፣ በውስጥ መስመር የሚወራው መረጃ እጅግ አስደንጋጭ ነው ተብሏል፡
ከክልሉና ከዞን ከፍተኛ አመራሮች ጋር በተደረገ ውይይት “ከዞን መምሪያ በላይ የመስከረም ወር ደመወዝ ጭማሬ ይከፈል” የሚል አቅጣጫ የተቀመጠ ቢሆንም እንዳልተፈፀመ ተገልጿል።
በታችኛው የወረዳ መዋቅር ያለው ክፍያ እንዲቆይ የተደረገው፣ “ለካድሬ ስልጣና ዓላማ የበጀት እጥረት ሊገጥመን ስለምችል እንጠቀማለን” በሚል ስሌት እንደሆነም ከታማኝ ምንጭ የተገኘ መረጃ የሚያመለክተው።
በዚህ አካሄድ የተነሳ፣ የመንግሥት ሠራተኞች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ መፈጠሩን በ WT Media ከተለያዩ ምንጮች የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ሠራተኞቹ “ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ለክልልና ለዞን መዋቅር የመስከረም ወር ውዝፍ መክፈሉ እሙን ነው፣ ነገር ግን በዞን ሥር ላሉ ወረዳና ከተማ መስተዳድር ዝምታን መርጠዋል! በመዋቅር እርከን የመብት ረገጣ አይሆንም ወይ?” በማለት በሕገወጥ የመብት ጥሰት ቅሬታ እያሰሙ ይገኛሉ።
ይህ የመስከረም ወር ጭማሪ ደመወዝ የተከለከለባቸው የወረዳ መዋቅር ሠራተኞች “ከዓመት ዓመት ከደመወዝ ውጭ ውሎ አበል የማይታሰበውን” ዋና ሥራ የሚሠሩ ናቸው።
በተቃራኒው፣ ውዝፍ ክፍያውን የሚከለክለው አመራር “ከቁርስ እስከ እራት በሥጋ ዘር መኖ እየበሉ” ስልጠናዎችን እንደሚከታተል መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ይህ የደመወዝ መከልከል ውሳኔ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አመራር ዘንድ ያለውን የመልካም አስተዳደር እጦትና የፍትህ መዛባት የሚያሳይ ሲሆን፣ በታችኛው መዋቅር ያለው የመንግሥት ሠራተኛ ላይ የሥነ ልቦናዊ እና የኢኮኖሚያዊ ጫና መፍጠሩ የማይቀር መሆኑ ተገልጿል።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media