የጌታቸው ረዳ የአልጀዚራ head to head ዝግጅት ቃለምልልስ ምን ይነግረናል… ? ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሳሳቱት የጌታቸው ዋጋ… የጌታቸው ዋጋ ስንት ነው ?
በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፣ የ WT Media መደበኛ ተጋባዥ ፀሃፊ
ጌታቸዉ ረዳ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ እጅግ ተጽዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኛ መሆኑ ግልጽ ነው። ለዚህ ካበቁት ምክንያቶች የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጥልቅ አረዳዱ፣ የንባብ ዝግጅቱ፣ የንግግር ብቃቱ እና ተጋፋጭነቱ እያልን መቀጠል እንችላለን። ባለፈዉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መጽሐፍ ሲመረቅ ከጸሐፊውና ሌሎች ምሑራን በእጅጉ በላቀ ሁኔታ የጌታቸዉ ንግግር እጅግ ብዙ እይታ ማግኘቱ አነጋጋሪ እንደነበረ ይታወሳል። ምናልባት በመለስ ዜናዊ ጀምሮ በኃይለማርያም ደሳለኝ የቀጠለዉን የአለም አቀፍ ሚዲያ ጋዜጠኞች ጋር የመጋፈጡን ነገር አሁን ላይ ጌታቸዉ ረዳ ብቻዉን ያስቀጠለም ይመስላል።
ቃለ ምልልሱ ላይ ጌታቸዉ በቀጥታ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ genocide በትግራይ ላይ ፈጽሟል ማለት አለመፈለጉ ብዙዎች አጋንነዉ ያዩት ይመስላል ምክንያቱም የፕሪቶሪያ ስምምነት መንፈስም አሁን ጌታቸዉ ያለበት ቦታም የሚፈልገዉን ነው ያደረገዉ።
ዋናዉ ና ወሳኙ ነገር ግን በትግራይ ሕዝብ ላይ የተፈጸሙትን ግፎች አንዳቸዉንም አለመካዱ ነው ፣በዚህም በድጋሚ ለትግራይ ሕዝብ ያለዉን ዉግንና አሳይቷል። በተለይ ከምዕራብ ትግራይ ጋር በተያያዘ ከፕሪቶሪያ ስምምነት ዉጭ የትኛውንም አቅጣጫ እንደማይከተል ማስረገጡም ይበል የሚያሰኝ ነው።

በተለይ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒሰትሩ ትልቅነት ላይ የሰጠዉ ምላሽ እጅግ ትክክለኛና የጌታቸው ዋጋ ከካድሬነት ከፍ ያለ መሆኑን ያስረገጠ ነው። ምክንያቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ “ጌታቸዉና እኔ አብረን ከሰራን…” በሚል የሰራዉን ፖለቲካ በሚገባ dilute ያደረገ ምላሽ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጌታቸው ግዙፍ እና ዉድ የፖለቲካ ስብዕና በእርካሽ መሸመታቸዉ ነበር፤ ጌታቸዉ በቃለምልልሱ ዋጋዉ እርካሽ እንዳልሆነ አስመስክራል።
ቢያንስ ገደል ማሚቱ ሳይሆን በራሱ አዕምሮ የሚያስብ መሆኑን አስመስክሯል፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእንግዲህ ጌታቸው ከካድሬዎቼ አንዱ ነው ብሎ ማሰቡ ስህተት እንደሆነ አሳይቷል። ከእንግዲህ ካባረረዉን ሌላ ማኖ ይነካል፣ ጌታቸዉና እኔ ብሎ ነግዷላ።
ይልቅ ግን ጌታቸዉ ተናግሮ ብዙ ትኩረት ያላገኘዉ ከእንግዲህ ለየትኛውም ስልጣን አልወዳደርም ያለበት ነው፣ ፓርቲም ያቋቋመዉ ለተለዬ ስልጣን አለመሆኑን ተናግሯል። በግሌ ግን ይሄ አልተዋጠልኝም፣ በቅድሚያ ይሄም ቢሆን ጌታቸው የስልጣንና ምቾት ጥም የሚያንገላታው ተራ ካድሬ አለመሆኑን ቢያሳይም፤ በዚህ ሰዓት ግን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ጌታቸው በግሌ መዉጣት አለበት ብዬ አላምንም።
ወዲ ረዳ ከእንግዲህ የኢትዮጵያ ፖለተካ ዉስጥ ሩጫውን የጨረሰ አይመስለኝም። በስምረት በኩል በትዉልድ አካባቢዉ ተወዳድሮ የፓርላማ አባል ቢሆን ምኞቴ ነው። በምርጫም፣ በሐገራዊ ምክክርም ሆነ በሌሎች መድረኮች ጌታቸዉ ያለዉን የንግግር ብቃት ተጠቅሞ የትግራይን ሕዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ ቢከራከር እጅግ መልካም ይመስለኛል።
የሕወሓትም ሰዎች ቢያንስ ከእንግዲህ እንደአንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኛ ቢቀበሉትና በክልሉ በነጻነት ቢንቀሳቀስ ለትግራይ ፖለቲካ አንድ አማራጭ ኃይል ነው። ጌታቸዉ ከእንግዲህ የሕዝብ አስተዳደር ስልጣን ካልፈለገም፣ የትምህርት ወይንም የጥናትና ምርምር ተቋማትን የመምራቱን ነገር፣ ቢያስብበት መልካም ነው።
በዚህ እድሜ ብዙ አቅም እያለዉ ጠቅልሎ ከፖለቲካ መዉጣት በፍጹም የለበትም። በተለይ የትግራይ ሕዝብ ጥቅም የማስከበሩ ሰላማዊ ትግል ከሚፈልጋቸዉ ሰዎች ጌታቸው ረዳ ግምባር ቀደሙ ነው።
ከዛ በተጨማሪ በአፋር ክልል ካሉ እራሳቸዉን፣ የትግራይ የሰላም ኃይል ብለዉ ከሚጠሩ ኃይሎች ጋር ግንኙነት የለኝም ማለቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ወዲ ረዳ ግን እነዚህ በሁለት ጎራ ያሉ የትግራይ ልጆች ወደ አንድነት እንዲመጡ የራሱን በጎ ሚና መጫወት ይጠበቅበታል።
መንገዶች ካሉት ታጣቂዎቹ ወደ ትግራይ ኮብልለዉ፣ ከወንድሞቻቸዉ ጋር ተቀላቅለዉ፣ የፕሪቶሪያ ስምምነትን ሙሉ ትግበራ ቢጠባበቁ ይበጃልና ያ የሚሆንበት መንገድ ካለ ብያስብበት ጥሩ።
ከዛ ባለፈ ትግራዋይ ሳይሆኑ ጌታቸው አምርረው የሚተቹ ሰዎች በአብዛኛው በሁለት ጎራ የሚከፈሉ ሲሆን አንደኛዎቹ የብልጽግና ምዕመናን ሲሆኑ ሁለተኛዎቹ በተለይ ከትግራይ ፖለቲካ ጌታቸው ከንግግር ችሎታዉና ተከራክሮ የመርታት አቅሙ ጋር እንዲወጣላቸው የሚፈልጉ ናቸው። ወዲ ረዳ አሁንም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ ደረጃቸዉ ከፍ ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ከሚከራከሩ ሰዎች አንዱ መሆን እንዳለበት እርግጥ ነው።
በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፣ የWT Media መደበኛ ተጋባዥ ፀሃፊ
ማሳሰቢያ ለአንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ( WT Media ) በዚሁ የፓለቲካ ወጌሻ እንግዳ ዝግጅት ላይ ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረበ የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን።