GridArt_20251224_170624568

በዎላይታ ዞን ኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ እና በጋሞ ዞን ቁጫ አልፋ ወረዳ መካከል የሚገነባውና የሁለቱ ሕዝቦች የዘመናት የልማት ጥያቄ የሆነው የደሜ ድልድይ ግንባታ፣ በዛሬው ዕለት በጋሞ ዞን በኩል በደረሰ ከፍተኛ ጫና እና በተቀነባበረ ሴራ ዳግም እንዲቆም መደረጉን WT Media አረጋግጧል።

ዛሬ ከቦታው ለ WT Media የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የድልድይ ግንባታው ሠራተኞች ከጋሞ ዞን በኩል በደረሰባቸው ማስፈራሪያና ጫና ምክንያት ሥራቸውን ለማቆም ተገደዋል።

ግንባታውን ለማስቆም በታቀደ ሴራ በድንጋይ ላይ “አንድም ሰው በዚህ አካባቢ እንዳይንቀሳቀስ” የሚል ትዕዛዝ በታፔላ ተጽፎ መለጠፉንና ይህም በሠራተኞቹ ላይ ከፍተኛ የደኅንነት ስጋት መፍጠሩ ተገልጿል።

ጨረታውን አሸንፎ ወደ ሥራ የገባው Prop Construction PLC በዎላይታ በኩል ያለውን የቁፋሮ ሥራ አጠናቆ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ለመሸጋገር ሲሞክር፣ በጋሞ በኩል የመጡ ኃይሎች በፈጠሩት ጫና ግንባታው እንዲስተጓጎል ተደርጓል።

ከሁለት ቀናት በፊት የዎላይታ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል አይሳሮ እና የኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ዋኬ ግንባታው መጀመሩን እንደ ታሪካዊ ስኬት ቢገልጹትም፣ በመሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ከዚህ በተቃራኒ ሆኗል።

የግንባታው ባለሙያዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት፣ ግንባታው ወደ ቁጫ ወረዳ እንዳይሻገር በክልል ከፍተኛ አመራሮች ትዕዛዝ እየተስተጓጎለ ይገኛል።

ዓላማው ተቋራጩ ተስፋ ቆርጦና ቅድመ ክፍያውን ሳይወስድ ሥራውን ጥሎ እንዲወጣ ለማድረግ የሚደረግ ስልታዊ ጫና መሆኑን ምንጮች ለ WT Media አረጋግጠዋል።

ለበርካታ ዓመታት ታቅዶና ተጀምሮ ሳይሳካ የዘለቀውን ይህን ፕሮጀክት፣ አሁንም በፖለቲካዊ ሴራ ለማደናቀፍ መሞከሩ “አሳፋሪ ተግባር” ነው ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ድልድዩ ከ15 በላይ ቀበሌያትን የሚያገናኝና ለማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር ወሳኝ መሆኑ እየታወቀ መሰናክል መፈጠሩ ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥሯል።

የአካባቢው ነዋሪዎችና የልማት ወዳዶች ይህንን በድፍረት የሚፈጸም የልማት ማደናቀፍ ተግባር የፌዴራል መንግሥትና የበላይ የመንግሥት አካላት በቅርበት እንዲመለከቱትና ጣልቃ ገብተው እንዲያስቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

WT Media ጉዳዩን አስመልክቶ ከጋሞ ዞንና ከክልሉ መንግሥት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት እስካሁን ባይሳካም፣ የግንባታውን ሂደትና የሚፈጸሙ ማናቸውንም መሰናክሎች በቅርበት መከታተሉን ይቀጥላል።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media