“ቅድሚያ ለሰብአዊ መብት በኢትዮጵያ” የተሰኘው መንግስታዊ ያልሆነ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት፣ በጦርነትና በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ባለመመለሱ እና አስፈላጊውን ድጋፍ ባለማድረጉ በፌዴራል መንግስት እና በክልል መስተዳድሮች ላይ ክስ መሰረተ።
ድርጅቱ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ችሎት የመሰረተው ይህ ክስ፣ አምስት ተከሳሾችን እንደሚያካትት ለWT Media የደረሰው የሰነድ መረጃ ያመለክታል።
እነሱም፦
- የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት
- የሰላም ሚኒስቴር
- የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት
- የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር
የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ናቸው።
በቀረበው የክስ ሰነድ መሠረት፣ ከህዳር 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ምክንያት ከምዕራብ ትግራይ እና ከአፋር ክልል ጭፍራ ወረዳ የተፈናቀሉ ከ 1,057,000 በላይ ዜጎች እስካሁን ወደ ቀያቸው አልተመለሱም።






እነዚህ ዜጎች በአማራ ክልል በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ እጅግ አስከፊ በሆነ የርሃብ፣ የድህነት እና የሞራል ውድቀት ውስጥ እንደሚገኙ ክሱ ያብራራል።
በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ከ 519,430 በላይ ዜጎች እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ወደ አማራ ክልል የተፈናቀሉ ከ 84,745 በላይ ዜጎች መጠለያ፣ ምግብ፣ ውሃ እና የጤና አገልግሎት አጥተው ለከፋ ስቃይ መዳረጋቸውን ድርጅቱ በዝርዝር አቅርቧል።
የተጣሱ ህጎች እና የቀረቡ ጥያቄዎች
ከሳሽ ድርጅት መንግስት በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 32 ላይ የተደነገገውን “ዜጎች በመረጡት የሀገሪቱ አካባቢ የመኖር መብት” ጥሷል ሲል ይከሳል።
እንዲሁም በካምፓላ ስምምነት (Kampala Convention) እና በኢትዮጵያ በጸደቀው አዋጅ ቁጥር 1187/2012 መሠረት ተፈናቃዮችን የመጠበቅ እና የመደገፍ ግዴታውን እንዳልተወጣ ጠቅሷል።
ከሳሽ ለፍርድ ቤቱ ያቀረባቸው ዋና ዋና ዳኝነት መጠየቂያዎች፦
- ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው የሚመለሱበት የደህንነት ዋስትና እና ተግባራዊ ስራ እንዲከናወን።
- ወደ ቀያቸው ሲመለሱ የወደሙ ቤቶቻቸው እንዲገነቡላቸው እና በቋሚነት እንዲቋቋሙ ትዕዛዝ እንዲሰጥ።
- የተፈናቀሉ ዜጎች በቂ የሰብአዊ እርዳታ (ምግብ፣ ህክምና እና መጠለያ) እንዲያገኙ እንዲደረግ የሚሉ ናቸው።
ድርጅቱ ለክሱ ማስረጃ ይሆኑ ዘንድ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ያወጣቸውን ሰነዶች እና የተለያዩ የዐይን እማኞችን ዝርዝር ለፍርድ ቤቱ አያይዞ አቅቧል።
ይህ ክስ በኢትዮጵያ በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች መብት መከበር ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media