በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሳውላ ካምፓስ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ተማሪ የሆነችው ባንቺይዝግዬ ደጀኔ በግል የማህበራዊ ሚዲያ ገጿ ባጋራችው መልዕክት ምክንያት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ገበታዋ እንድትታገድ መወሰኑን ለ WT Media የደረሰው የቪዲዮ መረጃ እና ለተማሪዋ የተሰጣት ቅጣት ውሳኔ ደብዳቤ ያመለክታል።
ዩኒቨርሲቲው መጋቢት 25/03/2018 ዓ.ም ባወጣው ይፋዊ ደብዳቤ እንደገለጸው፣ ተማሪዋ 17/03/2018 ዓ.ም በግል TikTok አካውንቷ ያስተላለፈችው መልዕክት “የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያውክ” እና “የመምህራንን ሞራል የሚነካ” ነው ተብሏል።
መልዕክቱ ተማሪዎች ለተቃውሞ እንዲነሳሱ የሚያደርግና በስነ-ልቦና ላይ ጫና የሚፈጥር ነው በሚል በዲሲፕሊን ኮሚቴ ቀርቧል።
ምንም እንኳ የዲሲፕሊን መመሪያው እስከ 3 ዓመት ስንብት ቢፈቅድም፣ ተማሪዋ ቀደም ሲል የዲሲፕሊን ሪከርድ የሌለባት በመሆኑ ለአንድ ዓመት ብቻ እንድትታገድ ተወስኗል።

እንደ WT Media የመረጃ ምንጮች ገለጻ፣ ተማሪዋ በ ቪዲዮው ያነሳችው ጥያቄ መምህራን ከ30 ደቂቃ በላይ ትምህርት ባይሰጡ የሚል ሲሆን፣ ይህም ከአካባቢው ከፍተኛ ሙቀት ጋር ተያይዞ ተማሪዎች ትኩረት ስለሚሳናቸው የቀረበ ጥያቄ ነው።
ይሁን እንጂ ውሳኔው እንዲፋጠን ያደረጉት የካምፓሱ አመራሮች መሆናቸው ተገልጿል። በካምፓሱ ውስጥ በሴቶች ዶርም የሚፈጸመውን የስልክ ስርቆት ተከትሎ ተማሪዎች ያነሱትን ተቃውሞ ለማዳፈንና ሌሎች ተማሪዎችን ለማስፈራራት ይህ ውሳኔ እንደ አጋጣሚ ጥቅም ላይ ውሏል ተብሏል።
የተማሪዋ የዲሲፕሊን ክስ የቀረበው 18 ቀን ሲሆን፣ ውሳኔው በአጭር ቀናት ውስጥ ተጠናቆ 22 ቀን ጸድቋል። ይህ ዓይነቱ የችኮላ ውሳኔ በዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራሮች ዘንድ ድጋፍ ባይኖረውም፣ በሳውላ ካምፓስ ኃላፊ ግትርነት ተግባራዊ መደረጉን ምንጮቻችን አረጋግጠዋል።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media