በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን ቦሎሶ ቦምቤ ወረዳ ውስጥ ባለፉት ጥቂት ቀናት የአምቡላንስ አገልግሎት ባለመኖሩ እና የሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በሰጡት አሳዛኝ ምላሽ ምክንያት የሁለት እናቶችና የአራት ህጻናት ህይወት ለአደጋ መጋለጡን ለ WT Media የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
ባለፈው አርብ ቀን 5፡30 ጀምሮ በምጥ ተይዛ የነበረችው ወ/ሮ አልማዝ በቀሌ፣ አስቸኳይ የአምቡላንስ ድጋፍ ብትፈልግም የወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት “አምቡላንስ የለም፣ ተበላሽቷል፣ ናፍጣ የለም” በሚሉ ምክንያቶች እስከ ምሽቱ 3፡00 ድረስ ድጋፍ ሳይሰጥ መቆየቱ ተገልጿል።
በእናቲቱ ማህፀን ውስጥ የነበሩት መንትያ ህጻናት አንደኛው በተፈጥሮአዊ መንገድ ለመውጣት ባለመቻሉና የእናቲቱ ህይወት ለአደጋ በመጋለጡ፣ በህብረተሰቡ ከፍተኛ ጩኸትና ወከባ ምክንያት ከምሽቱ 5፡30 ላይ በፖሊስ ፓትሮል መኪና ወደ ቦምቤ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተወስዳለች።


ሆኖም በእንግልቱ ምክንያት የእናቲቱን ህይወት ማትረፍ ቢቻልም የሁለቱን መንትያ ህጻናት ህይወት ማዳን አልተቻለም።
ይህ አሳዛኝ ክስተት በነጋታው በሌላ እናት ላይ ተደግሟል። ወ/ሮ ማብራት ቶማስ የተባሉ ነፍሰ ጡር እናት በምጥ ተይዘው በቃሬዛ እስከ መንገድ ዳር ቢመጡም፣ የአምቡላንስ ጥያቄ የቀረበላቸው የወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት ሃላፊ ስልክ ባለማንሳታቸው ረጅም ሰዓታት መጥፋቱ ተነግሯል።
የቀበሌው ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ለወረዳው አስተዳደር ስልክ ደውላ በነበረበት ወቅት፣ የአስተዳደሩ አካላት “ሌላ ልማት የላችሁም? በወሊድ ብቻ ነው እንዴ የምታውቁት?” በሚል የንቀትና የማስፈራሪያ ምላሽ እንደሰጧት ምንጮች ገልጸዋል።
በመጨረሻም በህብረተሰቡ ግፊት ከምሽቱ 2፡00 ላይ በፓትሮል መኪና ወደ ቦምቤ ሆስፒታል፣ ከዚያም ወደ ኦቶና ሆስፒታል ቢላኩም በደረሰባቸው የረጅም ሰዓት እንግልት (Delayed Delivery) ምክንያት እናቲቱና መንትያ ህጻናቱ ህይወታቸው አልፏል።
የአካባቢው ነዋሪዎች “ለህዝብ ደንታ የሌላቸው አስፈጻሚ አካላት” ሲሉ የሚገልጿቸው እነዚህ አመራሮች፣ እናቶች በህክምና እጦትና በቸልተኝነት እንዲያልቁ ማድረጋቸውን በምሬት እየገለጹ ይገኛሉ።
የወረዳው መንግስት ለእናቶች ህይወት ትኩረት እንዲሰጥና ተጠያቂነት እንዲሰፍንም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
WT Media የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የወረዳውና የዞኑን የጤና እና የአስተዳደር አካላት ምላሽ ለማካተት ጥረት እያደረገ ይገኛል።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media