በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በከፍተኛ ሙስና፣ በስልጣን መባለግና በንብረት ምዝበራ ስሙ ሲነሳ የቆየው የጋሞ ልማት ማህበር (ጋልማ) ዋና ስራ አስፈፃሚ ጨምሮ አራት ከፍተኛ አመራሮቹን ከኃላፊነት መነሳታቸው ተረጋግጧል።
ይሁን እንጂ የማህበሩ አባላትና ነዋሪዎች “የጥፋቱ ዋና ተዋናይና ራሳቸውን በህገ-ወጥ መንገድ ‘የበላይ ጠባቂ’ አድርገው የሾሙት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ሳይጠየቁ የሚደረግ የአመራር ለውጥ የሌብነት ማደባበሻ ነው” ሲሉ በጽኑ እየተቃወሙ ይገኛሉ።
ለ WT Media በደረሰው መረጃ መሠረት፣ የሚከተሉት የማህበሩ ከፍተኛ ኃላፊዎች ከቦታቸው እንዲወገዱ ተደርጎ በምትካቸው አዲስ የቅጥር ማስታወቂያም መውጣቱ ተረጋግጧል።
እንደ መረጃው ከሆነ ለዚህ ውዝግብ የበላይ ጠባቂ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ መሆናቸው እየታወቀ፣ አቶ ጥላሁን ከበደ ራሳቸውን “የበላይ ጠባቂ” አድርገው በመሾም ማህበሩን ለብልሹ አሰራር እያዋሉት ነው የሚለውን መዘገቡን ተከትሎ እርስበርስ አለመስማማት ውስጥ ስለመግባታቸው ከተነገረ በኃላ ነው።
ከኃላፊነት የተወገዱት ዶክተር ዋኖ ዋሎሌ- ዋና ስራ አስፈፃሚ፣ አቶ ደጉ ደሳለኝ- የበጎ አድራጎት ዘርፍ ኃላፊና ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ፣ አቶ ማሩ ሞታ-የቢዝነስ ዘርፍ ኃላፊና ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ፣ አቶ ሻምበል ሻኜ- የፋይናንስና የሰው ሀብት አስተዳደር ኃላፊና ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ እንደሆነም ተገልጿል።




WT Media ባለፈው ሳምንት የቀድሞ የቦርድ አባል አቶ ደሳለኝ ከበደ ካዛን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው፣ የጋልማ ትልቁ ችግር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ የፈጸሙት ስልጣን ነጠቃ ነው።
የማህበሩ ትክክለኛ የበላይ ጠባቂ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ መሆናቸው እየታወቀ፣ አቶ ጥላሁን ከበደ ራሳቸውን “የበላይ ጠባቂ” አድርገው በመሾም ማህበሩን የግል ጥቅማቸውን የሚያስከብሩበት የሙስና ማዕከል አድርገውታል ተብሏል።

ተቋሙን ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በቦርድ ሰብሳቢነትና አባልነት ለዘመናት በመቆጣጠር ለካድሬዎች መጫወቻና ለሀብት ብዝበዛ እንዲመች አድርገውታል ሲሉ በዝርዝር አጋልጠዋል።
አመራሮቹ ከመነሳታቸው ጋር ተያይዞ ከማህበሩ አባላት ዘንድ ብርቱ ተቃውሞና ጥያቄ እየቀረበ ይገኛል።
ሁሉንም ቅርንጫፎች፣ ዋና ቢሮውንና የቢዝነስ ዘርፉን በገለልተኛ አካል ኦዲት ተደርጎ ውጤቱ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ ተጠይቋል።
ያለ ቦርድ ውሳኔና ያለ ካሳ ለአሚባራ ሪል እስቴት፣ ለልዩነህ ዱባለ ትምህርት ቤትና ለጥቂት ግለሰቦች የተሰጠው ከ250 ሄክታር በላይ የጋልማ መሬት በአስቸኳይ እንዲመለስ አባላቱ አሳስበዋል።
“ግለሰቦችና ተቋማት መሬቱን በቅን ልቦና ተቀብለው ቢሆን እንኳ፣ ህግና አሰራርን በመጣስ የሰጣቸው አካል (አቶ ጥላሁን ከበደ) በህግ ሊጠየቁ ይገባል” የሚለው ሀሳብ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰማ ነው።
ርዕሰ መስተዳድሩ ተቋሙን ለሙስና ከመጠቀማቸው ባለፈ፣ በጋሞ ዞን ሻራ እና ዘይሴ አካባቢዎች ለተከሰቱት ግድያዎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እጃቸው እንዳለበት ቀደም ሲል የቀረበው ክስ አሁንም በብርቱ እየተነሳ ይገኛል።
በንጹሃን ላይ የተመሰረተው “የፈጠራ ክስ” እና በፖለቲካዊ ሴራ ሰዎችን ማሰቃየት በአስቸኳይ እንዲቆም ተጠይቋል።
WT Media ቀደም ሲል በርዕሰ መስተዳድሩ ዙሪያ ያቀረባቸው የምርመራ ዘገባዎች ዛሬ በተቋሙ ውስጥ በተወሰዱት እርምጃዎች መረጋገጣቸው የሚዲያችንን እውነተኝነት ያስመሰከረ ነው።
ሆኖም እርምጃው አራት አመራሮችን በማንሳት ብቻ እንዳይቀጭጭና ስር የሰደደው የርዕሰ መስተዳድሩ የሌብነት መረብ ከልማት ማህበሩ ባሻገር በክልሉ ያለውን ሌብነትና ብልሹ አሰራር አመላካች በመሆኑ የበላይ የመንግስት አካላትና የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገቡ ጥሪ እናቀርባለን። ጉዳዩንም በቅርበት መከታተላችንን እንቀጥላለን።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media