1000091162

በደቡብ ኢትዮጵያ ደመወዛቸውን የጠየቁ መምህራን በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን አመራሮች ግን በጉዳዩ ዙሪያ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ቁጫ አልፋ ወረዳ፣ ሕጋዊ የጥቅማጥቅም ጥያቄ ያነሱ መምህራን “በወረዳው አስተዳዳሪ ትእዛዝ” ለእስር መዳረጋቸውን ተከትሎ፣ የመማር ማስተማር ሂደቱ ሙሉ በሙሉ መቆሙን WT Media አረጋግጧል።

በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ የተጠየቁ የወረዳው አመራሮች ግን ዝምታን መርጠዋል።

በወረዳው የሚገኘው የቶኮ ዳምቢያ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን፣ መሠረታዊና ሕጋዊ የሆኑ የመብት ጥያቄዎችን በማንሳታቸው ለእንግልት ተዳርገዋል።

መምህራኑ የጠየቋቸው ነጥቦች፦ በ2018 ዓ.ም. የተደረገው የመስከረም ወር የደመወዝ ጭማሪ እስካሁን አለመከፈሉ፣ የ2014 ዓ.ም. ያልተከፈለ ውዝፍ ደመወዝና ጥቅማጥቅም እንዲከፈል የሚለው ይገኝበታል።

እንዲሁም በትምህርት ዝግጅታቸው መሠረት የሚገባቸው የደረጃ ዕድገትና የደመወዝ መተከል እንዲፈጸም የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ በወቅቱና በጊዜው እንዲከፈል የሚሉ ናቸው።

እነዚህን ጥያቄዎች ለወረዳው አስተዳደርና ለፓርቲ ጽሕፈት ቤት በሰላማዊ መንገድ በማቅረባቸው፣ የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ አስፋው አልኤና “እሰሩ” በሚል በሰጡት ቀጥተኛ ትእዛዝ መሠረት፣ 12 መምህራን ከታኅሣሥ 20/2018 ዓ.ም. ጀምሮ ለእስር ተዳርገዋል ብሏል።

  1. በግፍ የታሰሩ መምህራን ስም ዝርዝር 1 መ/ር አለፈ አድሴ
    2 መ/ር ሙሴ መና
    3 መ/ር ጥላሁን ኤልያስ
    4 መ/ር መለሴ አመሌ
    5 መ/ር አብርሃም ታንጋ
    6 መ/ር ተስፋዬ ታደሴ
    7 መ/ር ተመስገን ጌታቸው እና ሌሎች 5 አጠቃላይ 12 መምህራን መታሰራቸውን WT Media ከመምህራን ተወካይ እና ከቤተሰቦቻቸው አረጋግጠዋል።

WT Media የመምህራኑን መታሰርና የትምህርት ቤቱን መዘጋት አስመልክቶ የሚመለከታቸውን የወረዳው የሥራ ኃላፊዎች ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም፣ አመራሮቹ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ይህ የአመራሮች ዝምታና ኃላፊነትን የመሸሽ ተግባር በነዋሪዎችና በቤተሰቦች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል። በትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማር ሥራ ቆሞ ዛሬ 5ኛ ቀኑን ያስቆጠረ ሲሆን፣ ተማሪዎችም ያለ መምህር ሜዳ ላይ ቀርተዋል።

ሚዲያችን ቀደም ሲልም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች መምህራን ደመወዛቸው እየተቆረጠባቸውና ጥቅማጥቅማቸው እየተከለከሉ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲዘግብ መቆየቱ ይታወሳል።

በወቅቱ በሰራናቸው ዘገባዎች እንደተገለጸው፣ የአካባቢው አመራሮች የበጀት አስተዳደር ጉድለታቸውን ለመሸፈን ሲሉ ሕጋዊ ጥያቄ የሚያነሱ ዜጎችን በማሰርና በማስፈራራት ለማፈን መሞከራቸው የአሠራር ባህል እየሆነ መጥቷል።

አሁንም በቁጫ አልፋ ወረዳ የታየው ድርጊት የዚሁ ኢ-ሕገመንግሥታዊ አሠራር ቀጣይነት ነው።

WT Media የታሰሩ መምህራን በአፋጣኝ እንዲፈቱና ለተማሪዎች የመማር መብት ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪውን ያቀርባል። ጉዳዩን በቅርበት መከታተላችንን እንቀጥላለን።

የጭቁኖች ድምፅ – WT Media