የአቶ ጌታቸው ረዳ የአልጀዚራው የ “Head to Head” ፤ NBC ቆይታና ተያያዥ ጉዳዮች – በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፤ የ WT Media ተጋባዥ ጸሐፊ
አቶ ጌታቸው ረዳ ሰሞኑን በ NBC ቴሌቪዥን በሁለት ክፍል የቀረበ ቆይታ ማድረጋቸው ይታወሳል። ይህ ቃለ ምልልስ በአንድ በኩል የጋዜጠኛውን “አድራጊ ገጣሚነት” (ከኢሕአዴግ እስከ ብልጽግና ያለውን ሚና)፣ በሌላ በኩል ደግሞ የአቶ ጌታቸውን የአቋም መወላወል ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነበር።
አቶ ጌታቸው ከአልጀዚራው የ “Head to Head” ቆይታ በኋላ በአራት ኪሎ አካባቢ የተቀሰቀሰውን ንዴት ለማርገብና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመካስ የሞከሩበት ይመስላል።

ማሽቃበጥ ወይስ እውነታን መሸፋፈን?
በ NBC ቆይታቸው ጌታቸው ከመለሱት ጥያቄ ይልቅ የፈጠሩት ጥያቄ ይበልጣል። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማስደሰት ያደረጉት ጥረት “ውኃ የማይቋጥር” ሲሆን፣ በተቃራኒው የሕወሓት አመራሮችን የገመገሙበት መንገድ ግን በተሻለ እውነታ ላይ የተመሰረተ ነው።

ጌታቸው “የኢሳይያስ ዓላማ ግልጽ ነው” ቢሉም፣ ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ቀድመው ካወቁ ለምን ግንኙነቱን አላቋረጡም? ለምንስ በፓርላማ ጭምር የኤርትራን መንግሥት ሲያመሰግኑ ነበር? የሚሉት ጥያቄዎች የአቶ ጌታቸውን ትንታኔ ደካማ ያደርጉታል። የጌታቸው አቀራረብ አንዳንዴ የዳንኤል ክብረትን “የፈጠራ ወሬዎች” ይመስላል።
የሕወሓት የአመራር ድርቀት
ጌታቸው የሕወሓት አመራርን በሐሳብ ድርቀት መተቸቱ ተገቢ ነው። ከመለስ ዜናዊ ሕልፈት በኋላ ድርጅቱ ሁነኛ መሪ አለማግኘቱ እውነት ነው። አባይ ወልዱ “እንደ መለስ መጻፍ ይከብዳል” ማለታቸው፣ ዶ/ር ደብረጽዮንም በነባር አመራሮች (Old Guard) መዘወራቸውና ግልጽ አቅጣጫ አለማሳየታቸው ድርጅቱን ለውድቀት ዳርጎታል።
አሁንም ዶ/ር ደብረጽዮን የተሻለ አቅም ላለው ትግራዋይ አመራሩን ቢለቁ ይበጃል። ምናልባት ድርጅቱ በወቅቱ በአርከበ እቁባይና በዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ተመርቶ ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ መዳረሻ የተለየ በሆነ ነበር።
የመከላከያ “ሪፎርም” እና የዎላይታ ተወላጆች መገፋት
አቶ ጌታቸው ስለ መከላከያ ድክመት ያነሱት ነጥብ የብልጽግናን “ሪፎርም” ስህተት ያጋልጣል። ሹመትን በብሔር በማድረግ፣ በተለይም በጦሩ ውስጥ ከፍተኛ ልምድና ተሳትፎ የነበራቸውን የዎላይታና የትግራይ ተወላጆችን የመግፋት ውጤት ለብዙ ወታደሮች ሞት ምክንያት ሆኗል።
ጀነራሎችን ጨምሮ ወደ 40 ሺህ የሚጠጉ የዎላይታ ተወላጆች ከመከላከያ እንዲወጡ መደረጉ የጦሩን የመዋጋት አቅም አዳክሞታል። ዛሬ መንግሥት ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም ስልጣኑን ያጣውም በዚህ የአመራር ድክመት ምክንያት ነው።

የተፈናቃዮች ጉዳይና ቀጣይ ዕጣ ፈንታ
በተፈናቃዮች ጉዳይ ሕወሓትን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም። የፌዴራል መንግሥት ሕገወጥ አስተዳደሮችን ለምን አላፈረሰም? የፕሪቶሪያ ስምምነትስ ለምን ሙሉ በሙሉ አልተተገበረም? የሚሉት ነጥቦች ምላሽ ይፈልጋሉ።
በመጨረሻም፣ አቶ ጌታቸው የሕወሓትን አመራሮች “በማሸሟጠጥ” እና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ “በማሽቃበጥ” መካከል ያለው ሚዛን ወደ ማሸሟጠጡ ያዘነበለ ይመስላል። ይህም ምናልባት አሁን ባለው ሁኔታ የሕወሓት አመራሮችን መተቸት የተሻለ የነጻነት አየር ስለሚሰጠው ሊሆን ይችላል። በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚሰነዘረው “የወያኔ” ጥላቻም አገራዊ መፍትሔ የሚሻ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል።
በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና – የ WT Media ተጋባዥ ጸሐፊ