ከተጀምረ በኃላ ከ43 ዓመታት በላይ የቆየውና
ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው የጨንቻ-ሁምቦ ጠበላ የመንገድ ፕሮጀክት መቆሙ በማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ መፍጠሩ ተገልጿል።
WT Media በደረሰው መረጃ መሠረት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታንና ጋሞ ዞን የሚያገናኘው የጨንቻ-ሁምቦ ጠበላ የመንገድ ፕሮጀክት ጥያቄ ከተጀመረ 43 ዓመታትን ቢያስቆጥርም፣ እስካሁን ድረስ ምላሽ አጥቶ መቆየቱ የአካባቢውን አርሶ አደሮችና ነዋሪዎችን ለከፍተኛ ምሬትና እንግልት ዳርጓል።

የመንገዱ ግንባታ እንዲካሄድ ጥያቄ የቀረበው በ1975 ዓ.ም ሲሆን፣ በ1986 ዓ.ም ደግሞ በይፋ ስራው ተጀምሮ እንደነበር ይታወሳል።
አንደ መረጃው ከሆነ በወቅቱ የነበረው ፕሮጀክት ልዩ የሚያደርገው የአካባቢው አርሶ አደር የልማቱ ተሳታፊ ለመሆን “በነፍስ ወከፍ” ገንዘብ በማዋጣት ለግንባታው መፋጠን የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረከተ መሆኑ ነው።
ግንባታው ሲጀመር ከፌደራል እስከ ታችኛው የመንግስት መዋቅር ድረስ ያሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በታላቅ ተስፋ ነበር።
ሆኖም ግን፣ በወቅቱ ስራው በከፍተኛ መነሳሳት ቢጀመርም፣ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ግንባታው በድንገት ተቋርጦ እስካሁን ድረስ ለአራት አስርት ዓመታት ሳይቀጥል ቀርቷል።
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚገልጹት፣ መንገዱ ባለመሰራቱ ምክንያት ምርታቸውን ወደ ገበያ ለማውጣትና መሠረታዊ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት በእጅጉ ተቸግረዋል።
“ገንዘባችንን አዋጥተን፣ ተስፋ ተሰጥቶን ግን መንገዱ መሃል መንገድ ላይ መቅረቱ ፍትሃዊ አይደለም” የሚሉ ድምጾች በስፋት እየተሰሙ ይገኛሉ።
ይሄ የጨንቻ-ሁምቦ-ጠበላ መንገድ ፕሮጀክት ታሪክ የሚጀምረው ከ1950ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በተለያዩ አካላት ሲደረግ በነበረ የገንዘብ ማሰባሰብና ቅስቀሳ እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች ያስታውሳሉ።

በተለይም የኢህአዴግ መንግስት ስልጣን ከያዘ በኋላ፣ በወቅቱ አቶ ሽፈራው ሻሌ (ሟች) ሰብሳቢ የነበሩበት የመንገድ ሥራ አስተባባሪ ኮሚቴ በአገር ውስጥና በአዲስ አበባ ከሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ከፍተኛ ገንዘብ ማሰባሰቡን ነዋሪዎቹ በምሬት ይገልጻሉ።
እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ፣ በወቅቱ የመንገዱ ዲዛይን ተጠንቶና የግንባታ ማብሰሪያ ታፔላዎች በየቦታው ተተክለው የነበረ ቢሆንም፣ ለበርካታ ዓመታት ህዝቡ መንግስትን ሲጠባበቅ እነዚያው ታፔላዎች ተሰባብረው ከመቅረት ውጪ የተከናወነ ተግባር የለም።
ይህ መንገድ በጋሞ ዞን ብቻ አምስት ወረዳዎችን ማለትም፦ጨንቻ ከተማ ጨንቻ ዙሪያ ወረዳ፣ ዲታ ወረዳ፣ ቆጎታ ወረዳ እና ቦረዳ ወረዳን የሚያገናኝ ስትራቴጂካዊ አቋራጭ መንገድ ነው።
ለአምስት አስርት ዓመታት ያህል ጥያቄውን በሰላማዊና በጨዋ መንገድ ሲያቀርብ የቆየው የቦረዳ ህዝብ፣ አሁን ላይ ጥያቄው ወደ ወጣቱ ትውልድ መሸጋገሩን ገልጿል።
በተለይም ባለፉት ሶስት ዓመታት የአካባቢው ወጣቶች ጥያቄውን በተከታታይ ሲያቀርቡ የቆዩ ቢሆንም፣ ባለፉት ሶስት መንግስታት (ንጉሱ፣ ደርግና ኢህአዴግ/ብልጽግና) ለህዝቡ ጥያቄ ክብር ሰጥቶ ምላሽ የሚሰጥ አካል አለመገኘቱ ከፍተኛ ቅሬታ ፈጥሯል።
መንገዱ ወደ ዎላይታ፣ ወደ መካከለኛው ኢትዮጵያ ክልልና ወደ አዲስ አበባ ለመመላለስ አጭርና ተመራጭ ቢሆንም፣ እስካሁን በቸልታ መታለፉ የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በእጅጉ ጎድቶታል።
ማህበረሰቡ በእጃቸው ላይ የሚገኘውን ታሪካዊ ሰነድና ማስረጃ በመያዝ፣ የሚመለከተው የመንግስት አካል የቆመው ፕሮጀክት ዳግም የሚጀመርበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ጥያቄያቸውን በድጋሚ እያቀረቡ ይገኛሉ።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media