በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአስተዳደር ፍርድ ቤት ዳኞች ላይ የሚፈጸመው ጫና የፍትህ ሥርዓቱን እያፈረሰው መሆኑ ተገልጿል።
ከቀድሞ ደቡብ ክልል ጀምሮ በሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ስር የሚገኘው የአስተዳደር ፍርድ ቤት (ዎላይታ ምድብ ችሎት) በከፍተኛ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነትና በዳኞች ማዋከብ ምክንያት ስራውን በአግባቡ ማከናወን አለመቻሉ ተሰምቷል።
በተለይም ከ1,000 በላይ መምህራንን የሚመለከት የጥቅማ ጥቅም ጥያቄን ተከትሎ በዳኞች ላይ የሚደረገው ተጽዕኖ ፍርድ ቤቱን ለዝግጅት ዳርጎታል።
ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በብቃት ሲያገለግሉ የነበሩት ሰብሳቢ ዳኛ አቶ ሙሉነህ አስፋው፣ የካቢኔን ትዕዛዝ ባለመቀበላቸውና “ለመምህራን መብት መከበር አለበት” በማለታቸው ምክንያት ለተከታታይ ስደትና ጫና ተዳርገው፣ በሚያዚያ 2017 ዓ.ም ያለ ዕድሜያቸው በጡረታ እንዲገለሉ መደረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ሌሎች ዳኞች ያለምንም ህጋዊ አሰራር ከሥራ የተሰናበቱ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ፍርድ ቤቱ “ዳኛ የለም” በሚል ምክንያት አገልግሎት ማቆሙ ታውቋል።
በዚህ ምክንያት ያለ አግባብ ከሥራ የተሰናበቱ፣ ደመወዝ የተቋረጠባቸውና የአስተዳደር በደል የደረሰባቸው በርካታ የመንግሥት ሠራተኞች ጉዳያቸው ለወራት ሳይታይ ቀርቷል።
ተበዳዮች “ፍትህ አጥተን በየደጃፉ እያለቀስን ነው” ሲሉ ለWT Media ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
WT Media በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ለማግኘት ወደሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም፣ ኃላፊዎቹ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በፍትህ አካላት ላይ የሚፈጸመው ይህ አይነቱ ሕገ-ወጥ ጣልቃ ገብነት በአዲሱ ክልል አስተዳደር ላይ የሕዝብ አመኔታን እያሸረሸረ ይገኛል ተብሏል።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media