GridArt_20260112_174936669

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን በ2.44 ቢሊዮን ብር በጀት ሕዳር 2014 ዓ/ም የተጀመረው የወይቦ መስኖ ልማት ፕሮጀክት፣ በአሁኑ ወቅት ግንባታው ሙሉ በሙሉ ቆሞ ለከፍተኛ እንግልትና ለሀብት ብክነት መዳረጉን WT Media ያደረገው ጥልቅ ምርመራ አመላክቷል።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከ3,400 ሄክታር በላይ መሬት የማልማት አቅም ቢኖረውም፣ በሙስና ቅሌትና በአመራሮች ትኩረት ባለማግኘቱ ሳቢያ ዕጣ-ፋንታው ጥያቄ ውስጥ ወድቋል።

ከሁለት ዓመት በፊት WT Media ይፋ እንዳደረገው፣ በፕሮጀክቱ የካሣ ክፍያ ዙሪያ ዘግናኝ የሙስና ድርጊቶች ተፈጽመዋል።

በወቅቱ በተደረገ ማጣራት፦ በቦሎሶ ሶሬ ወረዳ የካሣ ክፍያ ከተፈጸመላቸው 401 አባወራዎች መካከል 76 የሚሆኑት ምንም ዓይነት ይዞታ የሌላቸው የአመራር ዘመዶችና ደላሎች መሆናቸው ተረጋግጧል።

በቦሎሶ ቦምቤ ወረዳ ደግሞ 56 ግለሰቦች በሕገ-ወጥ መንገድ ተመዝግበው የካሣ ክፍያ ወስደዋል።

የካሣ ግምቱ ከአመራሮችና ከደላሎች ጋር በመመሳጠር እስከ 1000% የዋጋ ግነት ተመዝግቦበታል።

በዚህ ዝርፊያ ውስጥ ከወረዳ እስከ ፌደራል ያሉ ከፍተኛ አመራሮች እጃቸው እንዳለበት ቢገለጽም፣ እስካሁን በምዝበራው የተሳተፉ ግለሰቦች ላይ የተረጋገጠ ሕጋዊ ተጠያቂነት አለመኖሩን የቅርብ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከአንድ ዓመት በፊት የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም በላይ በቦታው ተገኝተው ግንባታውን በአጭር ጊዜ ለማስቀጠል ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸው ነበር። ሆኖም ዛሬ ላይ እውነታው ተቀይሯል።

በወቅቱ ቃል የገቡት የክልልና የዞን አመራሮች በአሁኑ ወቅት ከኃላፊነታቸው ተነስተው ወደ ሌላ ቦታ ተዛውረዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልና የዎላይታ ዞን አስተዳደር አዲስ በወጣው አዋጅ መሠረት የ60/40 ድርሻቸውን ከፍለው የፕሮጀክቱን አካባቢ ከንክኪ ነፃ ማድረግ አልቻሉም።

በተለይ ክልሉ መክፈል ያለበትን 100 ሚሊዮን ብር ባለመክፈሉ ፕሮጀክቱ ታግዶ ይገኛል።

WT Media ከታማኝ የዜና ምንጮቹ እንደተረዳው፣ የካሣ ግምቱ ወጪ ከመጠን በላይ በመጨመሩ ፕሮጀክቱን ለመታጠፍ ሙከራ ተደርጎ ነበር።

የማልማት አቅሙን ከ 3,762 ሄክታር ወደ 2,000 ሄክታር ዝቅ በማድረግ የካሣ ክፍያውን ለመቀነስ የቀረበው የዲዛይን ማሻሻያ በክልሉና በዞኑ አመራሮች “ፕሮጀክቱ እንደነበረ ይቀጥል” በሚል ውድቅ ተደርጓል።

ይህ ውሳኔ ግን ለማህበረሰቡ በግልጽ አልተነገረም፤ ይልቁንም ካሣ ሳይከፈላቸው ከይዞታቸው የተነሱ አርሶአደሮች ለከፋ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ተዳርገው ይገኛሉ።

እንደ WT Media የመረጃ ምንጮች ትንታኔ፣ ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ እንዲመለስ የሚከተሉት እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል፦

  1. የክልሉና የዞኑ መንግሥት ድርሻቸውን (ካሣውን) በአፋጣኝ መክፈልና አካባቢውን ነፃ ማድረግ።
  2. የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ደካማ አፈጻጸም ያለውን ተቋራጭ ውል በማቋረጥ፣ አቅም ላለው አዲስ ተቋራጭ በጨረታ መስጠት።
  3. በካሣ ክፍያ ስም የተመዘበረው የሕዝብ ሀብት እንዲመለስና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግን ያካትታል።

የተጎጂ አርሶ አደሮች ድምፅ እና ወቅታዊ ሁኔታ
በፕሮጀክቱ ግንባታ ምክንያት ከይዞታቸው የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች በአሁኑ ወቅት የሚገኙበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን WT Media ያደረገው የመስክ ቅኝት ያመለክታል።

ለፕሮጀክቱ ግንባታና ለካናል ዝርጋታ ሲባል በመቶዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ከቤት ንብረታቸውና ከእርሻ መሬታቸው ቢፈናቀሉም፣ እስካሁን የሚገባቸውን የካሣ ክፍያ ባለማግኘታቸው ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል።

“መሬታችንን ለመንግሥት ሰጠን፤ አሁን ግን የምንበላው አጥተን ልጆቻችን ተርበዋል” ሲሉ አርሶ አደሮች ምሬታቸውን ገልጸዋል።

ለፕሮጀክቱ ሲባል ቤታቸው የፈረሰባቸው ቤተሰቦች መጠለያ አጥተው ለወራት በዘመድ ቤትና በኪራይ እየተንገላቱ ይገኛሉ።

አርሶ አደሮቹ በተደጋጋሚ ወደ ወረዳና ዞን አስተዳደር ቢሄዱም “በጀት የለም” እና “ተጠባበቁ” ከሚል ደረቅ ምላሽ ውጪ መፍትሔ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል።

“በእኛ ስም የመጣውን ገንዘብ ባለሥልጣናትና ደላሎች ሲከፋፈሉት እኛ ግን መሬታችንንም ካሣችንንም አጥተን ሜዳ ላይ ቀርተናል” ሲሉ አርሶ አደሮቹ ፍትሕ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

አሁን እየተባለ ካለው የካሳ መጠን መብዛት ይልቅ የወይቦ መስኖ ፕሮጀክት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ፈሶበት እንዲቆም የተደረገው በከፍተኛ የሙስና መረብ በመታጠሩና የአመራር ትኩረት በመነፈጉ ነው።

የአካባቢው አርሶ አደሮች የደረሰባቸው ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በአፋጣኝ እንዲፈታ፣ ለፕሮጀክቱ አስቸኳይ መፍትሔ ተሰጥቶ እንዲጀመር እና በሙስና የተሳተፉ አካላት ለሕግ እንዲቀርቡ WT Media ጥሪውን ያቀርባል።

በጉዳዩ ዙሪያ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው ያልተሳካ ቢሆንም ይሄንን ፕሮጀክትንና የተመዘበረውን የሕዝብ ሀብት ጉዳይ በዝርዝር መከታተሉን ይቀጥላል።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media