ሰበርመረጃ፦ የሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል አመራር ለቀረበላቸው ቅሬታ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ WT Media ለማዘጋት የ“ሪፖርት” ዘመቻ ከፈተ፤ ሠራተኞችንም እያገደ መሆኑ ተሰምቷል።
WT Media ባለፉት ቀናት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ በሚገኘው ሶዶ ክርስትያን ሆስፒታል (Soddo Christian Hospital) ውስጥ ያለውን መጠነ-ሰፊ ሙስና፣ የ85 ሚሊዮን ብር የታክስ ቅጣት እና የጤና ባለሙያዎች የደህንነት ስጋት ይፋ ማድረጉን ተከትሎ፣ የተቋሙ አስተዳደር ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ሚዲያውን ለማዘጋትና መረጃ ያወጡባቸዋል ያላቸውን ሠራተኞች ለማሳደድ አዲስ ዘመቻ መጀመሩን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ገብረስላሴ መረጃው ማፈትለኩን ተከትሎ ላለፉት ቀናት ተከታታይ የሆኑ ሦስት ዝግ ስብሰባዎችን ሲያካሂዱ መቆየታቸው ተሰምቷል።
በነዚህ ስብሰባዎች ላይ ለተነሱት ጥልቅ የሙስና እና የደህንነት ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፣ ትኩረቱ ዘገባውን ባወጣው WT Media እና መረጃ በሰጡ ሠራተኞች ላይ ያነጣጠረ እርምጃ መውሰድ እንደሆነ ታውቋል።

እንደ መረጃ ምንጮቻችን ገለጻ፣ አስተዳደሩ ሁለት ዋና ዋና ዘመቻዎችን (Challenges) በዛሬው ዕለት አስጀምሯል፦
የሆስፒታሉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) ባለሙያዎችንና የማህበራዊ ሚዲያ ተቆጣጣሪዎችን በመጠቀም፣ WT Media በፌስቡክና በሌሎች ገጾች ላይ የለጠፈው የምርመራ ዘገባ እንዲዘጋና ገጹ እንዲታገድ የ“Report” ዘመቻ ተጀምሯል።
በሆስፒታሉ የፋይናንስ ክፍል አማካኝነት የሆስፒታሉን እውነተኛ ገጽታ ለመሸፈን ያለመ የማህበራዊ ሚዲያ ንቅናቄ እንዲጀመር ታዟል።
ለዚህም እንዲውሉ የተቀረጹት መፈክሮች፦
“ሶዶ ክሪስቲያን ሆስፒታል ለመገልገል ሳይሆን ለማገልገል የሚሠራ! የኔ ሆስፒታል ነው! እጠብቀዋለው!”
“To serve, not to be served! It’s my Hospital! I stand with SCH” የሚሉ ናቸው።
አስተዳደሩ መረጃ አውጥተዋል ብሎ በጠረጠራቸው ሠራተኞች ላይ ከባድ ጫና እያደረሰ መሆኑ ተረጋግጧል።
ምንጮቻችን እንዳረጋገጡት፣ በአሁኑ ወቅት በርካታ ሠራተኞች የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እየደረሳቸው ሲሆን፣ የተወሰኑት ደግሞ ከሥራ የታገዱበት (Suspension) ሁኔታ አለ።
ይህ እርምጃ የሠራተኛውን የመብት ጥያቄ ለማፈንና ሌሎች ሠራተኞች ፍርሃት ውስጥ እንዲወድቁ ለማድረግ የታለመ መሆኑ ተገልጿል።
WT Media ከአሜሪካው የቦርድ አባል ኬን አምስተትዝ (Ken Amstutz) ጋር በነበረው የኢሜይል ልውውጥ፣ ሥራ አስኪያጁ አቶ ኤፍሬም ምላሽ እንዲሰጡ ዕድል እንዲሰጣቸው ቢጠይቅም፣ ሥራ አስኪያጁ ግን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የሃሳብ ነፃነትን ለማፈን መመረጣቸው የሚያሳዝን ነው።
ናትናኤል ጌቾ (WT Media መስራችና ዋና ኤዲተር) በጉዳዩ ላይ በሰጠው መግለጫ፦ “የሆስፒታሉ አመራር የሚዲያ ገጽ ለማዘጋት የሚጥረው እውነቱን መጋፈጥ ስለፈራ ነው። እኛ የሠራተኞችንና የታካሚዎችን ደህንነት የተመለከቱ መረጃዎችን በዝርዝር ማቅረባችንን እንቀጥላለን። የሚወሰደው የማስፈራሪያ እርምጃም ሆነ የሚዲያ ሪፖርት ዘመቻ ከእውነት አያቆመንም” ብሏል።
የሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል አመራር በሙስና፣ በታክስ ቅጣት እና በሠራተኞች ላይ በሚደርስ የጨረር አደጋ ዙሪያ የቀረቡበትን ከባድ ማስረጃዎች በማስተባበል ፈንታ፣ ወደ ማፈንና ማሳደድ መግባቱ ተቋሙ ያለበትን ቀውስ ይበልጥ አግዝፎታል።
የፌዴራል የጤና ባለሥልጣናትና የሚመለከታቸው የቁጥጥር አካላት፣ መረጃ ሰጪ ሠራተኞች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በአስቸኳይ እንዲያስቆሙና በሆስፒታሉ ውስጥ ባለው ብልሹ አሠራር ላይ ገለልተኛ ምርመራ እንዲያካሂዱ WT Media ጥሪውን በድጋሚ ያቀርባል።
እውነትን ማፈን አይቻልም!