በጎፋ ዞን በደረሰው አሰቃ'ቂ የመሬት መንሸራተት አደጋ

በደቡብ ኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በፊት በጎፋ ዞን በደረሰው አሰቃ’ቂ የመሬት መንሸራተት አደጋ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል። 

ይህን ተከትሎ ከሀገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ ለተፈናቀሉ ወገኖች የተሰበሰበውና ከ ግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የገንዘብና የቁሳቁስ እርዳታ የት እንደደረሰ እንደማይታወቅና በዞኑ ከፍተኛ አመራሮች መመዝበሩን ለ WT Media የደረሱን አዳዲስ ማስረጃዎች ያመለክታሉ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳግማዊ አየለ አደጋውን ተከትሎ የፈሰሰውን የሕዝብ እርዳታ ለግል ሀብት ማከማቻነት መጠቀማቸውና ወንጀሉን ለመሸፈን ተጠርጣሪዎችን እያሸሹ መሆናቸው ተጋልጧል።

1. ተጎጂዎች በረሃብ እያለቁ እርዳታው ተዘርፏል

በመሬት መንሸራተቱ ተጎጂ የሆኑ ወገኖች ዛሬም ድረስ መጠለያ አጥተውና በከፋ ችግር ውስጥ እያሉ፣ ለእነሱ ተብሎ የተሰበሰበው ሀብት በግለሰቦች ኪስ ገብቷል፦

  • የግማሽ ቢሊዮን ብር ጥያቄ፦ ከ60 ሚሊዮን ብር የባንክ ዝርፊያ ሙከራ ባሻገር፣ ከዓለም አቀፍ ለጋሾችና ከሀገር ውስጥ በዓይነትና በገንዘብ የተገኘውና ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት እርዳታ የገባበት አይታወቅም።
  • የተጎጂዎች ሁኔታ፦ አሁንም በመቶዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች የሚበሉትና የሚለብሱት አጥተው በከፋ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።

2. በአደጋው ስም የተገኘ የቤተሰብ ሀብት

አስተዳዳሪው አቶ ዳግማዊ አየለ አደጋው በደረሰ ጥቂት ወራት ውስጥ በቤተሰቦቻቸው ስም የናበረ ሀብት አፍርተዋል፦

  • የ 17 ሚሊዮን ብር ቤት፦ በአዲስ አበባ ከተማ በወንድማቸው (አቶ ምትኩ አየለ) ስም የተገዛ ቤት።
  • ተሳቢ መኪናዎች፦ በአማቾቻቸው ስም ሁለት አዳዲስ Trump ተሳቢ መኪናዎች።

3. ተጠርጣሪውን ዘመድ የማሸሽ ስውር ሴራ

የዝርፊያው ዋነኛ ተዋናይና የአስተዳዳሪው ባለቤት የአጎት ልጅ የሆነው አቶ ምህረቱ ዝናዬ፣ በዞኑ አስተዳዳሪ ልዩ ትዕዛዝ ከሕግ እንዲያመልጥ ተደርጓል። ፖሊስ አዲስ አበባ ላይ አግኝቶት እያለ “የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የለንም” በሚል ሰንካላ ሰበብ በአስተዳዳሪው የስልክ ትዕዛዝ እንዲለቀቅ ተደርጓል።

4. የኦዲት እምቢተኝነትና የታሰሩ ተጠርጣሪዎች

የዞኑ ምክር ቤት አባላት የአደጋ ሥጋት አካውንቱ ኦዲት እንዲደረግ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም፣ አስተዳዳሪው “አይደረግም” በማለት በኃይል ከልክለዋል።

በአሁኑ ወቅት በሳውላ ማረሚያ ቤት የሚገኙት እነ አቶ ተክለማርያም በቀለ (የጎፋ ዞን የፋይናንስ ኃላፊ)፣ አቶ ማርቆስ መለሰ (የአደጋ ሥጋት ኃላፊ) እና መሐመድ ከኔ (60 ሚሊዮን ብር የተጻፈበት ቼክ እጁ ላይ የተያዘ ግለሰብ) ሲሆኑ፣ እነዚህ ግለሰቦች እጅ ከፈንጂ ተይዘው ክስ ሳይመሰረትባቸው መቆየቱ የምርመራ ሂደቱን ጥያቄ ውስጥ ከቶታል።

በእነዚህ ግለሰቦች ላይ ለ5 ወራት ክስ ሳይመሰረት መቆየቱ፣ ዋናውን መሪ አቶ ዳግማዊ አየለን ለመሸፈን እንደሆነ ይገመታል።

የ WT Media ማሳሰቢያ

WT Media ከዚህ ቀደም በጎፋ ዞን የተፈጸመውን የ60 ሚሊዮን ብር ዝርፊያና ለጎርፍ አደጋ ተጎጂዎች የተሰበሰበው ገንዘብ መባከንን በተመለከተ ተከታታይ ዘገባዎችን መስራቱ ይታወቃል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የተቀበሩበትን የኬንቾ ሻቻን ሐዘን ተገን አድርጎ የተፈጸመው ይህ ዘረፋ በታሪክ የሚጠቀስ ከባድ ወንጀል ነው። WT Media የደረሱትን ሰነዶችና ማስረጃዎች በሙሉ ለሕዝብ ይፋ ማድረጉን ይቀጥላል። የፌደራልና የክልል የፀረ-ሙስና አካላት አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስዱ እንጠይቃለን።

የጭቁኖች ድምፅ – WT Media