የዎላይታ ሶዶ ኢንተርናሽናል ስታድየም ግንባታ ተጀመረ፤ “የኦቶና ሆስፒታልና ሌሎች እጣ እንዳይገጥመው” የሚሉ ስጋቶች ግን በርክተዋል።
የዎላይታን የስፖርት ታሪክና አቅም የሚመጥን፣ የፊፋ (FIFA) እና የካፍ (CAF) መስፈርቶችን የሚያሟላ ዓለም አቀፍ ስታድየም ግንባታ የመሠረተ ድንጋይ በዛሬው ዕለት ተቀምጧል።

ምንም እንኳ የፕሮጀክቱ መጀመር የስፖርት ቤተሰቡን ቢያስደስትም፣ ከዚህ ቀደም የተጀመሩና የገቡበት ያልታወቁ የልማት ፕሮጀክቶችን በማንሳት በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ የ”ግልጽነትና ተጠያቂነት” ጥያቄዎች እየተነሱ ነው።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እና የባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ የመሠረተ ድንጋዩን ባስቀመጡበት ወቅት እንደተገለጸው፦
ስታድየሙ ከ 45,000 በላይ ሕዝብ መያዝ የሚችል ሲሆን፣ ከሐዋሳ ኢንተርናሽናል ስታድየም ጋር ተመሳሳይ ዲዛይን አለው።
በላሾ ሳብስቴሽን አካባቢ በ 52 ሄክታር መሬት ላይ ያርፋል።
ግንባታውን ለማካሄድ የቻይናው CCCC ካምፓኒ ውል ገብቶ ሳይቱንና ዲዛይኑን ተረክቧል።
ዎላይታ በፕሪሚየር ሊግና በተለያዩ ዘርፎች የሚሳተፉ ከ 10 በላይ ክለቦችና ከ 500 በላይ ስፖርተኞች ያሉት በመሆኑ፣ የዚህ ስታድየም ግንባታ ለሀገርቱ ስፖርት ዕድገት ወሳኝ መሆኑ ታምኖበታል።

ምንም እንኳ የስታድየሙ ግንባታ ቢጀመርም፣ በዎላይታ ተወላጆችና በልማት ወዳዶች ዘንድ “የገቢ ማሰባሰቢያ አካውንት” ይፋ መደረጉ ጥርጣሬን ፈጥሯል።
ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቀሱት፦
በእሳት አደጋ የወደመውን ኦቶና ሆስፒታል ለመገንባት በሚል የተሰበሰበው ሀብትና ክልሉ የሰጠው 100 ሚሊዮን ብር የት እንደደረሰ እስካሁን ለሕዝብ ሪፖርት አልቀረበም።
የአረካ ሱማሞ አየር ማረፊያ፣ የወይቦ መስኖ ፕሮጀክት፣ የአባላ አባያ ሳመር ሲቲ እና የሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ግንባታዎች “የፎቶ ፖለቲካ” ሆነው መቅረታቸው ስጋቱን አባብሶታል።
የዎላይታ ልማት የተቀናጀ የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ሲምፖዚየም መካሄዱን ተከትሎ፣ ሕዝቡ ከፎቶ ባለፈ የሚከተሉት ነጥቦች በግልጽ እንዲመለሱ እየጠየቀ ይገኛል፦
የማርካቶ ገበያ ፕሮጀክትና የኦቶና ሆስፒታል የገቢ አሰባሰብ በገለልተኛ አካል ኦዲት ተደርጎ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ።
የስታድየሙ ጠቅላላ ግምት (Estimated Cost)፣ የሚጠናቀቅበት ጊዜ (Estimated Period) እና የገንዘብ ምንጩ በዝርዝር ለሕዝብ እንዲገለጽ።

ከስታድየም ግንባታ በፊት ለተጎዱ ወገኖች የጤና አገልግሎት የሚሰጠው የኦቶና ሆስፒታል ግንባታ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ሕዝቡ ድምፁን እያሰማ ነው።
WT Media የስታድየሙን ግንባታ ሂደትና የገቢ ማሰባሰቢያውን ግልጽነት በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎችን በቅርበት እየተከታተለ መረጃዎችን የሚያደርስ መሆኑን ይገልጻል።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media
R