ልዩ የምርመራ ዘገባ፦ የሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል ቀውስ – ከሙስና መረብ እስከ ሠራተኞች አፈና እና የጨረር ስጋት
በ ናትናኤል ጌቾ (WT Media መስራችና ዋና ኤዲተር)
በዎላይታ ምድር ለዓመታት የሕክምና ተስፋ ሆኖ የቆየው የሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል (Sodo Christian Hospital)፣ ዛሬ በታሪኩ አይቶት የማያውቀው ከፍተኛ አስተዳደራዊ እና ሰብአዊ ቀውስ ውስጥ ይገኛል።
WT Media ባለፉት ሳምንታት ተከታታይ የምርመራ ዘገባዎችን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ፣ የሆስፒታሉ አመራር የቀረቡበትን የሙስና እና የብልሹ አሠራር ማስረጃዎች ከመጋፈጥ ይልቅ፣ እውነቱን ለማፈንና ድምፃቸውን የሚያሰሙ ሠራተኞችን ለማጥፋት መጠነ-ሰፊ ዘመቻ መክፈቱን የደረሰን አዲስ መረጃ ያመለክታል።

1. የከሸፈው የሚዲያ ዘመቻ እና የሠራተኞች አፈና
WT Media ጥር 1 እና ጥር 4 ቀን 2018 ዓ.ም (Jan 09 & 13, 2026) ያወጣቸውን ዘገባዎች ተከትሎ፣ የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ገብረስላሴ ሦስት ተከታታይ ዝግ ስብሰባዎችን አድርገዋል። በነዚህ ስብሰባዎች የተወሰኑት እርምጃዎች ግን ተቋሙን ከማዳን ይልቅ ወደ ባሰ አፈና የሚወስዱ ሆነዋል፦
- የሚዲያ ዘመቻው መክሸፍ፦ አስተዳደሩ የሆስፒታሉን የIT ባለሙያዎች በመጠቀም የWT Media ገጽ እንዲዘጋ የ“Report” ቻሌንጅ አስጀምሮ ነበር። በተጨማሪም “እጠብቀዋለሁ፤ የኔ ሆስፒታል ነው!” በሚሉ መፈክሮች የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ቢከፍትም፣ ከእውነት ጋር መጋፈጥ ያልቻሉት የጥቅም ተጋሪዎች ዘመቻው ሳይሳካላቸው ቀርቶ አንድ በአንድ ማፈግፈግ ጀምረዋል።
- በሠራተኞች ላይ የተሰነዘረ ጡንቻ፦ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻው የከሸፈባቸው አመራሮች፣ አሁን ፊታቸውን ወደ ውስጥ ሠራተኞች አዙረዋል። “መረጃ አውጥታችኋል” በሚል ጥርጣሬ ብቻ፦
- ያለ አንዳች ማስጠንቀቂያ ደመወዝ ማገድ፤
- ከሥራ ፕሮግራም መሰረዝ፤
- ያለ በቂ ምክንያት ከሥራ ቦታ ማዛወር (Punitive Transfer) የመሳሰሉ ሕገ-ወጥ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ። ይህ እርምጃ በሠራተኛው ላይ ከፍተኛ የሥነ-ልቦና ስጋት የፈጠረ ቢሆንም፣ አስተዳደሩ ግን አሁንም ከሠራተኛው ጋር ተቀምጦ ቅሬታ ከመስማት ይልቅ የኃይል እርምጃን መርጧል።
2. የ85 ሚሊዮን ብር ቅጣትና የገንዘብ ምዝበራ
የተቋሙን ህልውና አደጋ ላይ የጣለው የፋይናንስ ምስቅልቅል አሁንም ምላሽ አላገኘም። የፌዴራል ታክስ ኦዲት የሐዋሳ ቅርንጫፍ መ/ቤት የጣለው ከ85 ሚሊዮን ብር በላይ ቅጣት ተደብቆ እንዲቆይ የተደረገ ሲሆን፣ ለጋሾች የሚልኩት ገንዘብም ለታለመለት ዓላማ ከመዋል ይልቅ ያለ ጨረታ ለሚከናወኑ ግዢዎችና ለጥቂት ግለሰቦች ጥቅም እየዋለ ነው። በተለይም ለጥገና የወጡ ውድ መሣሪያዎች ደብዛቸው መጥፋትና የሆስፒታሉ ነዳጅ ለግል ጥቅም መዋል አሁንም የቀጠለ አሳዛኝ ድርጊት ነው።

3. ለ10 ዓመታት የቀጠለው የጨረር (Radiation) ሰቆቃ
በዚህ የክትትል ዘገባ የተገኘው ሌላው አስደንጋጭ መረጃ፣ በኦፕሬሽን ክፍል ውስጥ ያለውን የጨረር አደጋ ይመለከታል።

- መከላከያ የሌለው ግንባታ፦ በThe United States Agency for International Development (USAID) ሙሉ ወጪ የተገነባው አዲሱ የቀዶ ጥገና ክፍል፣ ለጨረር ማሽኖች የሚሆን የጨረር መከላከያ (Lead lining) ሳይገጠምለት መገንባቱ ታውቋል።
- ያለ ባለሙያ የሚሰሩ ማሽኖች፦ ላለፉት 10 ዓመታት ሁለት የC-arm X-ray ማሽኖች በሙያው ባልሰለጠኑና የሙያ ፈቃድ በሌላቸው ግለሰቦች እንዲንቀሳቀሱ እየተደረገ ነው። ይህም የሠራተኛውንና የታካሚውን ተጋላጭነት በእጥፍ ጨምሮታል።
- የአመራሩ ጭካኔ፦ ለሠራተኞች የሚገባው የጨረር ተጋላጭነት ክፍያ ከመከልከሉም በላይ፣ የሥራ ደህንነት መሣሪያዎች (መነጽር፣ የታይሮይድ መከላከያ) በበቂ ሁኔታ አለመቅረባቸው የአስተዳደሩን ግልጽ ጭካኔ የሚያሳይ ሆኖ ተገኝቷል።
4. የባከኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ፈንዶች
ለእናቶችና ሕጻናት ተብሎ የተመደበው በጀት የት እንደደረሰ ሳይታወቅ፣ የ”Woman and Children’s – Hope Center” ግንባታ አሁንም በኮለን ደረጃ ቆሞ ይገኛል። ይህ ግንባታ የሙስና ምልክት ሆኖ ለዓመታት መቆየቱ፣ በዎላይታና አካባቢው የሚገኙ እናቶችን የሕክምና ተስፋ ያጨለመ ድርጊት ነው።


ማጠቃለያ እና የWT Media አቋም
የሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ገብረስላሴና የአሜሪካው ቦርድ አባል ኬን አምስተትዝ (Ken Amstutz) ስለ ጉዳዩ እንዲያውቁ ቢደረግም፣ እስካሁን ከዝምታና ከማፈን ውጭ መፍትሔ አልታየም።
WT Media የጭቁኖች ድምፅ የመሆን ኃላፊነቱን በመወጣት፣ ጉዳዩ መፍትሔ አግኝቶ ተጠያቂነት እስኪሰፍን ድረስ ዘገባውን ማቅረቡን ይቀጥላል።
- ለጤና ሚኒስቴርና ለኢትዮጵያ የጨረራ መከላከያ ባለሥልጣን፦ በኦፕሬሽን ክፍሉ ያለውን አደገኛ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲመረምሩ፤
- ለፀረ-ሙስና ኮሚሽን፦ በሆስፒታሉ ያለውን የ85 ሚሊዮን ብር ቅጣትና የግዢ ሥርዓት እንዲፈትሹ፤
- ለሕዝብ፦ ይህንን የታሪክ ሀብት ከጥፋት እንዲታደጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።