“የእንጨት ድልድይ ሰርተን ስንሻገር በውሃ ተበልተን እንለቅ፤ ታሪክም ይመዝገበን!” – የቡርጂ ዞን ነዋሪዎች የድረሱልን ጥሪ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘው የቡርጂ ዞን ህዝብ ከ60 ዓመታት (0.6 ክፍለ ዘመን) በላይ ምንም ዓይነት መሰረተ ልማት ሳይደርሰው፣ በመንግስት ተረስቶ በከባድ ስቃይ ውስጥ እንደሚገኝ ለWT Media ገልጹዋል።

ነዋሪዎቹ የመንገድ፣ የኔትወርክ እና የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎቶችን ማግኘት እንደ “ቅንጦት” የሚቆጠርበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።
የማህበራዊ አገልግሎቶች እጥረት እና የዜጎች እንግልት፦
- ትምህርት፦ ህፃናት ልጆች የትምህርት ተደራሽነት ፍለጋ በቀን ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ በእግር ለመጓዝ ተገድደዋል።
- ጤና፦ ነፍሰ ጡር እናቶች በቃሬዛ ተሸክመው ከ70 ኪሎ ሜትር በላይ እንዲጓዙ ይገደዳሉ። በዚህም ምክንያት “በጤና ተቋም ሲወልዱ እናት ጤና፤ ልጅም ደህና” የሚለው ሀገራዊ መፈክር ለዚህ አካባቢ ህዝብ ትርጉም አልባ ሆኗል።
- ወረርሽኝ፦ አካባቢው ለተለያዩ ወረርሽኞች (Pandemic) ተጋላጭ ሲሆን፣ በተለይም በኮሌራ ወረርሽኝ ወቅት ከፍተኛ የሰው ህይወት መጥፋቱ ይታወሳል።
ይህቺ በምስል ከታች የምትታየው እናት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡርጂ ዞን በመንገድና በጤና ጣቢያ እጦት ምክንያት ምጥ ይዟት የአከባቢው ወጣቶች በቃሬዛ ተሸክመው እየሄዱ በረሃ ላይ የወደቀች ናት!

የሰገን ወንዝ እና የህዝቡ የቆራጥነት እርምጃ፦
የአካባቢው አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ወደ እርሻቸውና ከብቶቻቸው ለመሻገር የሰገን ወንዝን ማለፍ ቢኖርባቸውም፣ ድልድይ ባለመኖሩ ለበርካታ ዓመታት ወንዙ የሰው ህይወት ሲቀጥፍ ቆይቷል።


በአሁኑ ወቅት የመንግስትን ምላሽ መጠበቅ የሰለቸው የቡርጂ ህዝብ፣ የራሱን ታሪክ በደም ላቡ ለመጻፍ ቆርጦ ተነስቷል። “የእንጨት ድልድይ ሰርተን ስንሻገር በውሃ ተበልተን አልቀን ሰማታትን እንቀላቀልና ታሪክ ሆኖ ይመዝገብልናል!” በሚል መሪ ቃል፣ በሰው ኃይል ድልድይ የመገንባት ስራ ላይ ይገኛሉ።
የአካባቢው ተወላጆች እና ነዋሪዎች መንግስት የዚህን ህዝብ ስቃይ አይቶ፣ ለዘመናት የቆዩ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን በአዎንታዊ መልኩ እንዲመልስ አጥብቀው ይጠይቃሉ።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media