በኢንፎሊንክ ኮሌጅ የተፈጸመው የገንዘብ ብዝበዛና ‘ሳልማር ተመረቅኩ’ በሚል የቀረበው አነጋጋሪ ቅሬታ፤ WT Media ያጠናቀረው ልዩ ዘገባ
በኢንፎሊንክ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የዎላይታ ሶዶ ካምፓስ ተማሪዎችና መምህራን በተቋሙ አስተዳደራዊ በደል፣ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ብዝበዛ እና ከፍተኛ የእንግልት ተግባራት እየተፈጸመብን ነው ሲሉ ለ WT Media አቤቱታ አቀርበዋል።
በተለይ ከቀናት በፊት በተካሄደው የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ዙሪያ የታዩ ግድፈቶች የተቋሙን አካዳሚክ ታማኝነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ጥለውታል።
1. የምረቃ ጋዋን እንደ “የንግድ ዕቃ”
የተቋሙ ተመራቂ ተማሪዎች ለምረቃ ጋዋን በሚል አለአግባብ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍሉ መገደዳቸውን መግለፁን በተመለከተ WT Media ከአንድ ወር በፊት መዘገቡ ይታወሳል።
በተጨማሪም ይህ ክፍያ ካለው ወቅታዊ የገበያ ዋጋ አንጻር እጅግ የተጋነነ መሆኑን ተማሪዎቹ ይናገራሉ።
ከዚህም በላይ ክፍያው በተቋሙ ሕጋዊ የባንክ አካውንት ሳይሆን በግለሰብ ስም በተከፈተ አካውንት እንዲገባ መደረጉ፣ አሠራሩ ለሙስና የተጋለጠና ግልጽነት የጎደለው መሆኑን ያሳያል ሲሉ ተማሪዎቹ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

2. መብታቸውን በጠየቁ ተማሪዎች ላይ የደረሰ “የፖሊስ ወከባ”
ተማሪዎቹ እነዚህን የአሠራር ግድፈቶች በጠየቁበት ወቅት፣ የኮሌጁ አስተዳደር የጸጥታ ኃይሎችን (ፖሊስ) ወደ ግቢው በማስገባት ተማሪዎችን እንዲበተኑና ወደ ግቢው እንዳይገቡ ሲያስፈራራ እንደነበር ታውቋል።

WT Media የፖሊስ አባላት ተማሪዎችን ሲያባርሩና ግቢውን ሲዘጉ የሚያሳይ የቪዲዮ መረጃ ከቦታው ደርሶታል።
3. “ሳይማሩ መመረቅ” እና የአካዳሚክ ጥራት ጥያቄ
በተለይ ከፍተኛ መነጋገሪያ የሆነው ጉዳይ፣ አንድ ተመራቂ ተማሪ “ሳልማር ነው የተመረቅኩት” በማለት በቪዲዮ የሰጠው ምስክርነት ነው።
ይህ ተማሪ በዎላይትኛ ቋንቋ ባስተላለፈው መልዕክት፦ “ብርሃኑ ነጋ ሆይ! ይኸው ሳልማር ተመርቄያለሁ፣ ተቃጠል” በማለት በትምህርት ጥራት ላይ ያለውን ከፍተኛ ክፍተት ከማሳየት ባሻገር ገንዘብ የከፈለ ማንኛውም ግለሰብ ሳይማር ድግሪና ማስተርስ ወረቀት ማግኘት ይችላል በሚል የደረሰን መረጃ አረጋግጦ አጋልጧል።
WT Media በደረሰው ተጨማሪ መረጃ መሠረት፣ ይህ ተዘግቦ የነበረው የተመራቂ ተማሪዎችና ሌሎች ቅሬታ ያነሷቸው ጥያቄዎች ሳይፈቱ በጥር 23 ቀን 2018 ዓ.ም በዎላይታ ሶዶ ከተማ እንዲመረቁ ተደርጓል።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተመረቁት ተማሪዎች ጠቅላላ ቁጥር አለመገለጹ፣ ተቋሙ “ሳይማሩ ገንዘብ የከፈሉትንም ጭምር” እያስመረቀ ነው የሚለውን ጥርጣሬ አጠናክሮታል።
4. የመምህራን ብዝበዛና እንግልት
የተቋሙ መምህራንም ለ WT Media በሰጡት ቃል፣ ኮሌጁ ከተማሪዎች ገንዘብ ቢሰበስብም ለመምህራን ክፍያ ላይ ግን “ስርዓት የጎደለው” አሠራር ይከተላል ብለዋል።
- መምህራን ኮርሱን አስተምረው ውጤት ካስገቡ በኋላ ክፍያ የሚከለከሉበት ሁኔታ መኖሩ፣
- በሲስተም እና በዋይፋይ (WiFi) ብልሽት ምክንያት መምህራን ተገኝተው እያስተማሩ “አልተመዘገባችሁም” በሚል ደመወዝ መከልከላቸው፣
- በአንድ ክፍል ውስጥ እስከ 100 ተማሪዎች በማጨቅ ለትምህርት ጥራት ትኩረት አለመስጠቱ በዋናነት ተጠቅሷል።
5. የተቋሙ ምላሽ
WT Media የቀረቡትን ከባድ ውንጀላዎች በተመለከተ የኢንፎሊንክ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የዎላይታ ሶዶ ካምፓስ አመራሮችን እና የዋናውን መሥሪያ ቤት ባለሥልጣናትን በግል ስልክና በመደበኛ መስመር ለማግኘት በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም፣ አመራሮቹ ስልክ ባለማንሳታቸውና ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሙከራው ሳይሳካ ቀርቷል።
WT Media የጭቁን ተማሪዎችንና መምህራንን ድምፅ ለማሰማት ጉዳዩን በቅርበት መከታተሉን ይቀጥላል።
ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በተነሱ ቅሬታው ዙሪያ ለጊዜው ምላሽ ባይሰጡም ይሄንን ዘገባ ተከትሎ የሚሰጡ ከሆነ ምላሻቸውን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናችንን እንገልፃለን።
የሚመለከታቸው የትምህርት ጥራት ቁጥጥር አካላትና የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዚህ “ሕገ-ወጥ” አሠራር ላይ አስቸኳይ ማብራሪያ እንዲሰጡና የተማሪዎችና መምህራን በደል እንዲቆም እንጠይቃለን።
🎙️ WT Media – የጭቁኖች ድምፅ!