Zeyse Genocide

የዘይሴ ብሔረሰብ የዘመናት የማንነትና የመዋቅር ጥያቄ፤ በክልሉ አመራሮች እየተፈጸመ ያለው የሰብዓዊ መብት ረገጣና የጭቆና ቀንበር

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዘይሴ አርሶ አደሮች ላይ የተከፈተው ጥቃት ቀጥሎ፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና የተጎጂ ቤተሰቦች በከፍተኛ ስጋትና እንግልት ውስጥ መሆናቸውን ለ WT Media በሰጡት ቃል ገልጸዋል። ጥቃቱ የታቀደና “የዘይሴን አርሶ አደር ከማሳው ለማፈናቀል” ያለመ ነው ሲሉ እማኞቹ ይከሳሉ።

“አስክሬን ለመውሰድ ሄደን ሌላ ሞት ገጠመን”

ከስፍራው ያነጋገርናቸው አንድ የሟች ቤተሰብ በለቅሶ የታጀበ ቃላቸውን እንዲህ ሰጥተዋል፦

“ልጆቻችን ለቀን ሥራ ሄደው ነው የተገደሉት። አንደኛውን አስክሬን በዘይሴ አርሶ አደሮች እርዳታ አግኝተን ለመውሰድ ስንሞክር፣ የጸጥታ አካላት አሁንም ተኩስ እየከፈቱብን ነው። በየቀኑ ወደ ማሳችን እየገቡ ሥራችንን እንዳንሠራ ከማድረጋቸው በላይ፣ ልጆቻችንን እንደ አውሬ እያደኑ እየገደሉብን ነው።”

በአሁኑ ወቅት ከስድስት በላይ አርሶ አደሮች መገደላቸው የተረጋገጠ ሲሆን፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ወጣቶች ደግሞ የት ደረሱ? የሚለው እስካሁን ምላሽ አላገኘም።

  • የአስክሬን ሁኔታ፦ እስካሁን የአንዱ ወጣት አስክሬን ያለበት ቦታ አለመታወቁ ቤተሰቦችን ለከፋ ስቃይ ዳርጓል።
  • የቀን ሠራተኞች ስጋት፦ ራሳቸውን ሰርተው ለመለወጥ ከ “ሜሌ” ጋጉሌ ቀበሌ የመጡ ወጣቶች ያለምንም ጥፋት ለጥቃት መጋለጣቸው፣ በሁለቱ አጎራባች ሕዝቦች መካከል የነበረውን ሰላማዊ ግንኙነት ለማሻከር የሚደረግ ሴራ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ነዋሪዎች ድርጊቱን “መንግስታዊ ሽብርተኝነት” ብለው የሚጠሩት፣ ጥቃቱ የሚፈጸመው ሕዝብን ሊጠብቅ በሚገባው የክልሉ ጸጥታ ኃይልና የጋሞ ዞን መደበኛ ፖሊስ በመሆኑ ነው። “ፖሊስ አጥፊን መያዝ ሲገባው፣ አርሶ አደርን በማሳው ላይ መግደል ከጀመረ ማንን እንመካለን?” ሲሉ አርሶ አደሮቹ ይጠይቃሉ።

WT Media የተረጋገጡ መረጃዎችንና የሰነድ ማስረጃዎችን በመያዝ የሚከተሉትን ነጥቦች በድጋሚ ያሳስባል፦

  1. ለፌዴራል ፖሊስና መከላከያ፦ በክልሉ ጸጥታ ኃይልና በአርሶ አደሩ መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት በአስቸኳይ ቆሞ፣ ገለልተኛ አካል አካባቢውን እንዲጠብቅ።
  2. ለሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፦ በዘይሴ አርሶ አደሮች ላይ የደረሰውን ግድያና የጠፋውን አስክሬን ጉዳይ በአስቸኳይ እንዲመረምር።
  3. ለክልሉ አመራሮች፦ የጸጥታ ኃይሉን ከአርሶ አደሩ ማሳ ላይ በማስወጣት፣ ለጠፋው ሕይወትና ለደረሰው ጉዳይ ተጠያቂነት እንዲሰፍን።

WT Media የዘይሴ ሕዝብ የሚያደርገውን መራር ትግልና እየደረሰበት ያለውን የዘር ማጥፋት (Genocide) ድርጊት በተደጋጋሚ ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። እውነትና ፍትሕ እስኪነግሥ ድረስ ለጭቁኑ የዘይሴ ሕዝብ ድምፅ መሆናችንን አጠናክረን እንቀጥላለን።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media