GridArt_20260204_211617785

በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢ ውስጥ በተለያዩ የንግድ ስራዎች ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 19 የኢንተርፕራይዝ ማህበራት፣ ከስምንት ወራት በላይ ከስራ ገበታቸው ተፈናቅለው በከፍተኛ እንግልት ላይ እንደሚገኙ ለWT Media ገልጿል።

ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ “ጊዜያቸውን የጨረሱ ማህበራትን ወደ ቀጣይ ምዕራፍ የማሸጋገር ስራ ነው” ሲል ለቀረበው ቅሬታ ምላሽ ሰጥቷል።

Official Wolaita Sodo University Logo

ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት፤ በሰኔ ወር 2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ደህንነትን ለመጠበቅ ሲባል “ለአንድ ወር ብቻ ግቢውን ለቃችሁ ቆዩ” የሚል መመሪያ ተሰጥቷቸው ወጥተዋል።

ሆኖም ፈተናው ተጠናቆ ወደ ስራቸው ለመመለስ ሲሞክሩ በዩኒቨርሲቲው ጥበቃና አመራሮች “ያለ ማኔጅመንት ውሳኔ መግባት አትችሉም” በሚል ተከልክለዋል።

“የልጆቻችን ቀለብና የቤት ኪራይ መክፈያ አጥተን በከፍተኛ ችግር ላይ እንገኛለን” የሚሉት ማህበራቱ፣ በተለይም የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ተክለ ሌዛ ሆን ብለው የዞኑን የስራ እድል ፈጠራ መመሪያ ወደ ጎን በመተው አፈናቅለውናል” ሲሉ ይከስሳሉ።

የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ተክለ ሌዛ

ዶክተር ተክለ በሰጡት ምላሽ፦ “ዩኒቨርሲቲው ለበርካታ ዓመታት አነስተኛ ማህበራትን በመቀበል የምግብ ዋስትናቸውን ሲያረጋግጥ ቆይቷል። አሁን ውሳኔ የተላለፈባቸው አብዛኞቹ ማህበራት በመመሪያው መሰረት በግቢው ውስጥ የሚቆዩበትን ህጋዊ ጊዜ ያጠናቀቁ ናቸው” ብለዋል።”>

አክለውም፣ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ ማህበራት ወደ ዞኑ ተመልሰው ወደ ቀጣይ የሽግግር ምዕራፍ መሄድ እንዳለባቸውና ደንብ የሚያከብሩ ማህበራት ግን አሁንም በግቢው ውስጥ እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።

“ቀሪዎችም እየተጣራ የሚፈጸም ይሆናል” ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

እንደ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገለጻ፣ የዎላይታ ዞን ስራ እድል ፈጠራና ክህሎት መመሪያ ከሰባት ጊዜ በላይ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር ተነጋግሯል።

መመሪያው “ማህበራቱ በህገ-ወጥ መንገድ መውጣት የለባቸውም፣ በራሳቸው እግር እስኪቆሙ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል” የሚል አቋም ቢይዝም፣ ዩኒቨርሲቲው “እኛ የምንመራው በፌዴራል ደንብ ነው” በሚል የዞኑን አመራር ሳይቀበል መቅረቱ ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት 19 ማህበራትና በመቶዎች የሚቆጠሩ የቤተሰብ አባላት ለስምንት ወራት ያለ ስራ ተቀምጠዋል።

ዩኒቨርሲቲው “ህግና መመሪያ እየተከተልኩ ነው” ቢልም፣ ማህበራቱ ግን “በፈተና ሰበብ በሴራ ተፈናቅለናል” የሚለውን አቋማቸውን ይዘዋል።

WT Media በጉዳዩ ዙሪያ የሚደረጉ ቀጣይ ክትትሎችንና የሚሰጡ ውሳኔዎችን ለተመልካቾቹ ማድረሱን ይቀጥላል።

️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን

Voice of Marginalized Community – WT Media