በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ከአንድ ዓመት በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ያለቁበትን የመሬት መንሸራተት አደጋ ተገን በማድረግ የተፈጸመው ግዙፍ የሀብት ምዝበራ፣ አዲስ ምዕራፍ ላይ መድረሱ ተገልጿል።
WT Media በተከታታይ ሲያጋልጥ የነበረውን ይህን ወንጀል ለማድበስበስና ማስረጃ ለማጥፋት በዞኑ ከፍተኛ አመራሮች የሚመራው ሴራ ቢቀጥልም፣ ዛሬ የፌዴራል ኦዲተሮች ቡድን ሳውላ መግባቱ ተረጋግጧል።

የምዝበራው ዋና መሪ መሆናቸው በምስክሮች የተጠቀሱት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳግማዊ አየለ፣ ወንጀሉን ለመሸፈን አዲስ ሴራ መጎንጎናቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
አቶ ዳግማዊ ከሳውላ ከተማ ከንቲባ ጋር በመመሳጠር፣ ከመንግሥት ቋት ከ500,000 ብር በላይ ለጉቦ ወጪ በማድረግ፣ ሁለት የሕግ አካላትን (መርማሪ እና ዓቃቤ ሕግ) ወደ ማረሚያ ቤት ልከዋል” የሚል ታማኝ መረጃ ለWT Media ደርሷል።
ቁልፍ ተጠርጣሪው አቶ መሐመድ ኑርሁሰን ቀደም ሲል በአስተዳዳሪው ላይ የሰጠውን እውነተኛ ቃል እንዲቀይር፣ “ቃሌን በስህተት ነው የሰጠሁት” ካለ በአጭር ጊዜ እንዲፈታና ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ እንዲፈጸምለት ድርድር እየተደረገ ይገኛል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሕዝብን እሮሮ ተከትሎ የፌዴራል ኦዲት ኮርፖሬሽን ባለሙያዎች ቡድን በዛሬው ዕለት ሳውላ ከተማ መግባታቸው ታውቋል።
ኦዲቱ የሚከተሉትን ነጥቦች ያጠቃልላል ተብሎ ይጠበቃል፦
– የ60 ሚሊዮን ብሩ ቼክ ማጭበርበር፦ በአቶ መሐመድ ኑርሁሰን ስም ተጽፎ የነበረው ቼክና ከጀርባው ያሉ ባለሥልጣናት ሚና።
– የአንድ ቢሊዮን ብር ሀብት፦ ከአገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ ለጋሾች ለኬንቾ ሻቻ ተጎጂዎች የተሰበሰበውና ወደ አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋው ጥሬ ገንዘብና የዓይነት እርዳታ ያለበት ደረጃ።
ባለፉት ሳምንታት “ወንጀሉን አጋልጣችኋል” በሚል በፖሊስና ዓቃቤ ሕግ የተያዙ ከ20 በላይ ሰዎች አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ።

የታሰሩት ግለሰቦች እስካሁን ፍርድ ቤት አልቀረቡም፤ ይባስ ብሎም አስተዳዳሪው መረጃ ያቀብላሉ ያላቸውን ተጨማሪ ሰዎች ለማሰር አደን ጀምረዋል።
አቶ ዳግማዊ ጉዳዩን ገለልተኛ አካል እንዳይይዘው በማድረግ፣ መረጃዎችን የማጥፋትና ወንጀሉን በንጹሐን ላይ የማላከክ ሥራ በሰፊው እየሠሩ መሆኑ ተረጋግጧል።
ይህን በቢሊዮን የሚቆጠር የሕዝብ ሀብት የዘረፉና ማስረጃ ለማጥፋት የሚደራደሩ ባለሥልጣናት ለሕግ እንዲቀርቡ WT Media የጀመረውን የሚዲያ ሽፋን አጠናክሮ ይቀጥላል።

የፌዴራል ኦዲት ኮርፖሬሽን ኦዲተሮች ቡድን በነፃነት ሥራውን እንዲሠራና ተጠርጣሪው አቶ መሐመድ ኑርሁሰን ወደ ፌዴራል ማረሚያ ቤት ተዛውሮ ደህንነቱ እንዲጠበቅ እንጠይቃለን።
ይህን ታሪካዊ የሌብነት ሴራ በንቃት እንድትከታተሉና ማስረጃዎችን ለሚመለከተው አካል እንድታደርሱ ጥሪ እናቀርባለን።
️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን
Voice of Marginalized Community – WT Media