GridArt_20260207_150702893

የዎላይታ የቀድሞ ተማሪዎች ማህበር ዛሬ ጥር 30 ቀን 2018 ዓ.ም ባካሄደው ጉባኤ በይፋ መመስረቱንና የስራ አስፈፃሚ ቦርድ አባላትን መምረጡን አስታውቋል።

ማህበሩ በኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሠረት የተቋቋመ ሲሆን፣ ታዋቂ ግለሰቦችን በሊቀመንበርነት መርጧል።

በጉባኤው ውሳኔ መሠረት የሚከተሉት ግለሰቦች የማህበሩን የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ እንዲመሩ ተሰይመዋል፡-

1. አምባሳደር ዶ/ር ተሾመ ቶጋ – ሰብሳቢ
2. ፕሮፌሰር ሰለሞን ሶርሳ – ምክትል ሰብሳቢ
3. አቶ ማቴዎስ ባልቻ – ጸሐፊ
4. አቶ አማኑኤል አብርሃም – የሕዝብ ግንኙነት
5. ዶ/ር ተሾመ ታከለ – ሂሳብ ሹም

በተጨማሪም ወ/ሮ አበበች ጎዳና፣ አቶ አልታየ አየለ፣ ዶ/ር አብርሃም አሳሮ እና አቶ ደሳለኝ እናሮ በቦርድ አባልነት ሲመረጡ፤ አቶ ታረቀኝ ታፈሰ፣ ዶ/ር ታምራት በለጠ እና ዶ/ር ማርቆስ ጩምቡሮ የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚቴ ሆነው ተመርጠዋል።

WT Media ባደረገው ማህበራዊ ሚዲያ ቅኝት ማህበሩ መመስረቱ ቢታወቅም፣ በአካባቢው ምሁራንና ወጣቶች ዘንድ ግን አደረጃጀቱንና አስፈላጊነቱን አስመልክቶ ብርቱ ትችቶችና ጥያቄዎች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ።

በዋናነት የተነሱት ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፡-

“የቀድሞ ተማሪዎች” የሚለው ስያሜ የትኛውን ዘመን እንደሚወክል ግልጽ አለመሆኑና አውዱን የሚያጠብ በመሆኑ፣ በምትኩ “የዎላይታ ጠቅላላ ምሁራን ፎረም” በሚል ተዋቅሮ ልምድ ያላቸው አባቶች ለወጣቱ እውቀት የሚያጋሩበት ቢሆን ይሻል ነበር የሚሉ አስተያየቶች በስፋት እየተደመጡ ነው።

ቀደም ሲል ተመስርቶ የነበረው የዎላይታ የምሁራን ማህበር የት ደረሰ? አዲሱ ማህበርስ ከቀድሞው ምን የተለየ ዓላማ ሰንቆ መጣ? የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ይሻሉ።

በአሁኑ ወቅት በዎላይታ ከ200 ሺህ በላይ የተማሩ ስራ አጥ ወጣቶች ባሉበት ሁኔታ፣ የ”ጡረተኞች” ማህበር መመስረት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ወይ? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው። ወጣቶቹ በራሳቸው ተደራጅተው ለመፍትሄ ቢታገሉ ውጤታማ እንደሚሆኑም ይነገራል።

ምርጫ ከመቃረቡ ጋር ተያይዞ፣ “ለአምስት ዓመታት አካባቢውን ዘንግተው የቆዩ ግለሰቦች በየሰበቡ ብቅ እያሉ ነው” የሚሉ ስጋቶች በማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ እየተንጸባረቁ ይገኛሉ።

WT Media ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ከማህበሩ አመራሮች በኩል የተሰጠ ዝርዝር ዓላማና መመሪያ ካለ ተከታትሎ የሚያቀርብ ይሆናል።

️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን

Voice of Marginalized Community – WT Media

Read more on our official website