"ሳልማር ተመረቅኩ" ያለውን በመቀየር “ጸጽቶኛል” በሚል ሌላ ቃል ሰጠ - በኢንፎሊንክ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በተማሪዎችና መምህራን ላይ እየደረሰ ነው ከተባለውን “ብዝበዛ፣ እንግልትና ጥራት መጓደል” በተጨማሪ አሁን ላይ የታየው አዲስ ለውጥ
በዚሁ በኢንፎሊንክ ዩንቨርስቲ ኮሌጅ በተማሪዎችና መምህራን ላይ እየደረሰ ነው ከተባለውን “ብዝበዛ፣ እንግልትና ጥራት መጓደል” ባሻገር “ሳልማር ተመረቅኩ” ያለው ተማሪ ቪዲዮውን ማንሳቱ በተቋሙ ላይ ተጨማሪ ጥያቄ ማንሳቱ ተገልጿል።
ተማሪው ቪዲዮውን ያነሳው በገዛ ፈቃዱ ይሁን ወይም በኮሌጁ አስተዳደር ግፊት የታወቀ ነገር የሌለ ሲሆን ምንም እንኳን ጉዳዩ በማህበራዊ ሚዲያ ከፍተኛ መነጋገሪያ ቢሆንም፣ የኢንፎሊንክ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አስተዳደር እስካሁን ለዚህና ለሌሎች ቅሬታዎች በይፋ የሰጠው ማብራሪያ የለም።

WT Media ባለፉት ሁለት ቀናት በኢንፎሊንክ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የዎላይታ ሶዶ ካምፓስ ተማሪዎችና መምህራን ላይ እየደረሰ ነው የተባለውን የገንዘብ ብዝበዛ፣ እንግልት እና የአካዳሚክ ጥራት መጓደል በተመለከተ ዝርዝር ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል።
በቀደመው ዘገባችን ያነሳናቸው ዋና ዋና ነጥቦች፦ ተማሪዎች ለምረቃ ጋዋን ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍሉ መገደዳቸውና ክፍያውም በግለሰብ አካውንት እንዲገባ መደረጉን፤
መምህራን ላባቸው ሳይከፈላቸው ለወራት መቆየታቸውንና በሲስተም ብልሽት ምክንያት ደመወዝ እንደሚከለከሉ፤ እንዲሁም ተማሪዎች መብታቸውን በጠየቁበት ወቅት በፖሊስ ኃይል መባረራቸውን የሚያሳይ የቪዲዮ ማስረጃ ማቅረባችን ይታወሳል።
በቀደመው ዘገባችን ላይ “ሳልማር ተመርቄያለሁ” በሚል በቪዲዮ ቀርቦ የነበረው ተመራቂ ሞገስ አኔቦ፣ አሁን ላይ ቪዲዮውን ከማህበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ማንሳቱን WT Media አረጋግጧል።
ከአረካ ከተማ አቅራቢያ የሚኖረው ይህ ተማሪ፣ በዎላይታ ሶዶ ከተማ ኮሌጁ ከሚገኝበት ቦታ ራቅ ብሎ በሰራው የመጀመሪያ ቪዲዮ ላይ የኮሌጁ ስም የታተመበትን ጋዋን እና የመመረቂያ ሰነድ (Bind Cover) በመያዝ ተቋሙን ሲተች ታይቶ ነበር።

ሆኖም ግን፣ ተማሪው አሁን ላይ “ይህንን ቪዲዮ በመስራቴ ጸጽቶኛል” የሚል ማስተባበያ ሰርቶ መልቀቁን ተመልክተናል። ይህ የተማሪው የሃሳብ መቀየር ያጋጠመው፣ ጥር 23 ቀን 2018 ዓ.ም የኮሌጁ የምረቃ ስነስርዓት ከተከናወነ በኋላ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው።
ምንም እንኳን ተማሪው “ጸጽቶኛል” ቢልም፣ WT Media በቀደመው ዘገባው ያነሳቸው የመዋቅር እና የፋይናንስ ብልሽት ጥያቄዎች ግን አሁንም ምላሽ አላገኙም።
በምረቃው ስነስርዓት ላይ ምን ያህል ተማሪዎች እንደተመረቁ አለመገለጹ፣ ተቋሙ በጥራት ላይ ሳይሆን በገንዘብ ብቻ ላይ ትኩረት አድርጓል የሚለውን ጥርጣሬ አጠናክሮታል።
WT Media ባለፉት ቀናት ለኮሌጁ ዋና አመራሮችና ለዎላይታ ሶዶ ካምፓስ ኃላፊዎች በግል ስልካቸው ጭምር በመደወልና መልዕክት በመላክ ምላሽ ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም፣ ተቋሙ እስካሁኑ ሰዓት ድረስ በይፋም ሆነ በግል የሰጠው ምንም ዓይነት ምላሽ የለም።
የተማሪው ቪዲዮውን ማንሳት በኮሌጁ ውስጥ ያሉትን ሌሎች መሰረታዊ ችግሮች (የመምህራን ክፍያ እና የገንዘብ ብዝበዛ) አይፈታቸውም። WT Media የተጨቆኑ ተማሪዎችንና የመምህራንን ድምፅ በማሰማት እውነት እስኪወጣ ድረስ ጉዳዩን በቅርበት መከታተሉን ይቀጥላል።
የሚመለከታቸው የትምህርት ጥራት ቁጥጥር አካላትና የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዚህ “ሕገ-ወጥ” አሠራር ላይ አስቸኳይ ማብራሪያ እንዲሰጡና የተማሪዎችና መምህራን በደል እንዲቆም እንጠይቃለን።