GridArt_20260209_163713182

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በዎላይታ ዞን፣ ቦዲቲ ከተማ የምክር ቤቱ የ’ስያሜ ለውጥ’ ውሳኔ እና በትምህርት ጥራት ላይ የተጋረጠው ቀውስ – ዝርዝር ዘገባ

በዎላይታ ዞን የቦዲቲ ከተማ ምክር ቤት በቅርቡ ባካሄደው 4ኛ ዙር 13ኛ የስራ ዘመን መደበኛ ጉባኤ፣ ቀደም ሲል የ’ቦዲቲ መለስ ዜናዊ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት’ ተብሎ ይጠራ የነበረውን ተቋም ስያሜ ወደ ‘ብርጋዲየር ጀነራል ዶክተር ጋጋ ኦልጆ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት’ እንዲቀየር በሙሉ ድምፅ መወሰኑ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ውሳኔው ታሪክን ከመተካት ውዝግብ ባለፈ፣ በትምህርት ቤቱ እጅግ አሳሳቢ የትምህርት ጥራት ዝቅጠትና የተቋሙ የህልውና አደጋ ላይ ትልቅ ጥያቄ አስነስቷል።

ምክር ቤቱ የወሰነው የስያሜ ለውጥ በህዝብ አስተያየትና በማህበራዊ ሚዲያ ምልከታዎች “ታሪክን በማክበር እና ታሪክን በመተካት መካከል ያለውን ስስ መስመር የጣሰ ታሪካዊ ስህተት ነው” በሚል ጠንካራ ተቃውሞ እየገጠመው ይገኛል።

ብርጋዲየር ጀነራል ዶክተር ጋጋ ኦልጆ ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ባለውለታ መሆናቸው ባያከራክርም፣ ተቺዎች ግን “የአንዱን ጀግና ታሪክ ለመዘከር የሌላውን ታሪክ መፋቅ አስፈላጊ አይደለም” ሲሉ ይሞግታሉ።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የታሪክ አሻራ በቦታው ሊጠበቅ እንደሚገባና ጀግንነትን ለማስታወስ አዲስና ዘመናዊ ተቋማትን መገንባት የተሻለ መንገድ እንደነበር ተገልጿል።

ውሳኔው በስያሜ ዙሪያ በሚነሱ ውዝግቦች ቢጠመድም፣ WT Media ያሰባሰበው መረጃ ግን የተቋሙን አሳዛኝ ውስጣዊ ገጽታ ያጋልጣል።

ትምህርት ቤቱ ስያሜ ከመቀየር ባለፈ፣ ዜጋን የመቅረጽ ተልዕኮውን ሙሉ በሙሉ ስቷል የሚያሰኙ መረጃዎች ተገኝተዋል፦

በመረጃው መሠረት ከ2014 እስከ 2017 ዓ.ም ባሉት ዓመታት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ 1,771 ተማሪዎች መካከል ዩኒቨርሲቲ መግባት የቻሉት 4 (አራት) ወንዶች ተማሪዎች ብቻ ናቸው።

ለአብነትም በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ከ9ኛ-12ኛ ክፍል ያሉት ተማሪዎች ቁጥር 350 ብቻ ሲሆን፣ የሚያስተምሯቸው መምህራን ቁጥር ግን ከ150 በላይ ነው። ይህ ማለት ለአንድ መምህር በአማካይ ሁለት ተማሪ ብቻ ይደርሳል ማለት ነው።

ለነዚህ ጥቂት ተማሪዎች 150 መምህራንና 19 የአስተዳደር ሰራተኞች ደመወዝ እየተከፈለ መሆኑ፣ ዞኑና ከተማው በትምህርት ጥራትና በተቋሙ ህልውና ላይ ከመስራት ይልቅ በስያሜ ጉዳይ መጠመዳቸው ትዝብት ላይ ጥሏቸዋል።

ትምህርት ቤቱ በ2005 ዓ.ም የተመሰረተበት መነሻ ምክንያት “የመታሰቢያ” ዓላማ ብቻ እንደነበር ይነገራል።

ተቋሙ የተገነባው በተለምዶ ‘ዋላጫ’ በሚባል ከከተማ ወጣ ባለ፣ መሠረተ ልማት ባልተሟላበት፣ በገደልና በወንዝ ዳር በሚገኝ ጫካ ውስጥ ነው። ይህ ተገቢ ያልሆነ ስፍራ ተማሪዎችን በተለይም ሴቶችን ለከፋ አደጋ (ደፈራ) አጋልጧል።

በአሁኑ ወቅት ትምህርት ቤቱ መግቢያና መውጫ መንገድ የሌለው ከመሆኑም በላይ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደዚህ ተቋም ለመላክ ባለመፈለጋቸው ትምህርት ቤቱ የመዘጋት አደጋ ተደቅኖበታል።

የቦዲቲ ከተማ ምክር ቤት የስያሜ ለውጡን ያደረገበትን በቂ ምክንያት ለWT Media ባይገልጽም፣ የተቋሙ ወቅታዊ ሁኔታ ግን ከስም መቀየር በላይ ስር ነቀል የጥራትና የደህንነት ማሻሻያ እንደሚፈልግ ያሳያል።

ታሪክን ከመፋቅ ይልቅ የተሻለ ትውልድ መቅረፅ ለሀገር የሚበጅ መንገድ መሆኑን ተቺዎች ያሳስባሉ።

️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን

Voice of Marginalized Community – WT Media