GridArt_20260209_201133654

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጎፋ ዞን የኬንቾ ሻቻ የመሬት መንሸራተት አደጋ ተጎጂዎችን ለመርዳት የተሰበሰበውን ወደ አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ሀብት ምዝበራ በተመለከተ “ወንጀሉን አጋልጣችኋል” በሚል የታሰሩ ወጣቶች ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

WT Media እጃቸው የገባውን የፍርድ ቤት ሰነዶች መነሻ በማድረግ ባደረገው ምርመራ፣ ተጠርጣሪዎቹ ላይ የቀረበው ክስና የምርመራ ሂደት የፍትሕ ሥርዓቱን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ሆኖ ተገኝቷል።

ፖሊስ “በሐሰተኛ ማኅበራዊ ሚዲያ (Fake Account) ቀስቃሽ ጽሁፎችን በመፃፍና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ የጥላቻ ንግግር በማሰራጨት” ወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ በማለት ለፍርድ ቤት ያቀረባቸው 10 ግለሰቦች የሚከተሉት ናቸው፦

መልካሙ ኡታ፣ እያሱ በላቸዉ፣ ፍሬዉ አየለ፣ ምንዳዬ ይርዳዉ፣ አክልሉ ወልቃ፣ ከበደ ካሳ፣ ሰማዬ ሻምበል፣ ውብነህ እያሱ፣ ሰለሞን ባርዳሞ እና ስንታየሁ ታደሰ የተባሉ ወጣቶች በአንድ መዝገብ ቀርበዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ምርመራ ቡድን ለጎፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባቀረበው አቤቱታ፣ ተጠርጣሪዎቹ በክልሉ በተለያዩ ዞኖች ከሚገኙ ግለሰቦች ጋር ትስስር አላቸው በሚል በተደጋጋሚ የጊዜ ቀጠሮ ሲጠይቅ ቆይቷል፦

ከ24 ባንኮች የገንዘብ እንቅስቃሴ መረጃ ማጣራት፣ የተያዙ ስልኮችና ላፕቶፖችን በመረጃና ደህንነት ተቋም ማስመርመር፣ እንዲሁም የ5 ምስክሮችን ቃል መቀበል የሚሉ ነጥቦች በሰነዱ ላይ ተጠቅሰዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ወንጀሉን በማጋለጣቸው ብቻ መታሰራቸው እየታወቀ፣ ፖሊስ “አካባቢው እንዳይረጋጋና መንግሥት ወደ ልማት ሥራው እንዳይገባ አመኔታ ለማጣት ሠርተዋል” በሚል የፖለቲካ ክስ እንዲመስል ማድረጉ ነዋሪዎችን አስቆጥቷል።

በማረሚያ ቤት የሚገኘው ቁልፍ ተጠርጣሪ አቶ መሐመድ ኑርሁሰን፣ ቀደም ሲል በአስተዳዳሪው አቶ ዳግማዊ አየለ ላይ የሰጠውን ምስክርነት እንዲቀይር በከፍተኛ ገንዘብ ድርድር እየተደረገበት መሆኑ ተጋልጧል።

የሳውላ ከተማ ከንቲባ ዶክተር ንጉሰ መኮንን እና የዞኑ አስተዳዳሪ በመመሳጠር ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ፣ መርማሪዎችንና ዓቃቤ ሕግን በመላክ ምስክርነቱን በገንዘብ ለመግዛት እየሞከሩ ይገኛሉ።

ከ20 በላይ የሚሆኑት ታሳሪዎች እስካሁን ፍርድ ቤት ሳይቀርቡና መብታቸው ሳይከበር በጨለማ ቤት ውስጥ እንደሚገኙ የ WT Media ምንጮች አረጋግጠዋል።

​በአንድ መዝገብ የተከሰሱት 19 ተጠርጣሪዎች በአሁኑ ወቅት በሚከተሉት የፖሊስ ጣቢያዎች ተከፋፍለው ይገኛሉ፦

​በሳውላ ፖሊስ ጣቢያ፦ 9 ሰዎች
​በመሎ ወረዳ ላሃ ፖሊስ ጣቢያ፦ 7 ሰዎች
​በደምባ ጎፋ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ፦ 3 ሰዎች
​እነዚህ ዜጎች “መንግስት እንዳይረጋጋ አድርገዋል” እና “ለተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች (WT Mediaን ጨምሮ) መረጃ ሰጥተዋል” በሚሉ ምክንያቶች ለእስር ተዳርገዋል።

​በደምባ ጎፋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ያዕቆብ ደበላ ላይ የቀረበው ክስ እጅግ አስደንጋጭ ነው። አስተዳዳሪው ተጠርጥሮ የታሰረው የ አቶ ውብነህ ኢያሱ ቤት በአካል በመሄድ፣ ለባለቤታቸው የሚከተለውን የዛቻ ቃል ተናግረዋል፦

​”ባለቤትሽ ከምርጫ በፊት ከእስር አይወጣም፤ ልጆችሽን ብቻሽን ለማሳደግ ራስሽን አዘጋጂ!” ​ይህ ድርጊት ፍርድ ቤት ባልወሰነበት ጉዳይ አስተዳዳሪው ራሳቸው “ፈራጅ” በመሆን በቤተሰብ ላይ ከፍተኛ የስነ-ልቦና ጦርነትና ማሸበር መፈጸማቸውን ያሳያል።

​ሌላው ተጠርጣሪ አቶ አክልሉ ወልቃ ቤት የሄዱ 8 የደምባ ጎፋ ወረዳ ፖሊሶች፣ ምንም ዓይነት የፍርድ ቤት የብርበራ ትዕዛዝ ሳይዙ ቤቱን መበርበራቸው ተረጋግጧል።

በወቅቱ ቤት የነበረችው የተጠርጣሪው ባለቤት በፖሊሶች ዛቻ በመደንገጧ፣ ቤቷን ጥላ ወደ ቤተሰቦቿ ለመሰደድ ተገዳለች።
​
​ተጠርጣሪዎቹ ለ WT Media ባደረሱት መረጃ መሠረት፣ የዞኑ አመራሮች “እነዚህ ወንጀለኞች ናቸው፤ እነሱን የሚጠይቅ አካል ክትትል ይደረግበት” የሚል ትዕዛዝ በማስተላለፍ ወዳጅ ዘመድ እንዳይጠይቃቸውና ሕዝቡ ፍርሃት ውስጥ እንዲገባ እያደረጉ ይገኛሉ።

ይህ ድርጊት በሕገ-መንግሥቱ የተደነገገውን የመጠየቅና የሕግ ጥበቃ የማግኘት መብትን በግልጽ የጣሰ ነው።

እነዚህ ዜጎች “ሙስናው ይመርመር” በማለታቸው ብቻ ታስረውና ቤተሰቦቻቸው እየታደኑ ባለበት ወቅት፣ የፌዴራል ኦዲት ኮርፖሬሽን ባለሙያዎች ሳውላ መግባታቸው ለፍትሕ ፈላጊው ሕዝብ ትልቅ ተስፋ ነው ተብሏል።

ኦዲተሮቹ ወደ አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋውን የሟቾች እርዳታ እና የ60 ሚሊዮን ብር የቼክ ማጭበርበሩን ይመረምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
​
​የጎፋ ዞን አመራሮች የቢሊዮን ብር ምዝበራውን ለመሸፈን ሲሉ የፍትሕ ሥርዓቱን ወደ “የግል መሣሪያነት” ለውጠውታል።

​ለፌዴራል መንግሥት፦ በፖለቲካ በቀል የታሰሩት 19  እና እየተፈለጉ የሚገኙ ዜጎች በአስቸኳይ እንዲፈቱና በቤተሰቦቻቸው ላይ ዛቻ የፈጸሙ አስተዳዳሪዎች ለሕግ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን።

​ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፦ በሳውላ፣ ላሃና ደምባ ጎፋ ፖሊስ ጣቢያዎች የሚገኙ እስረኞች ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲመረመር ጥሪ እያቀረብን የዚህን ግዙፍ የምዝበራ ወንጀልና ሰብዓዊ መብታቸው ተጥሰው የታሰሩና የቤተሰቦቻቸው ስደትና ወከባ ሁኔታ መከታተሉን ይቀጥላል።

️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን

Voice of Marginalized Community – WT Media