የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢንስፔክሽንና የውስጥ ኦዲት ቁጥጥር አገልግሎት ሰሞኑን ያወጣው የግማሽ ዓመት ሪፖርት፣ በክልሉ ያለውን የሀብት ምዝበራ፣ የአሰራር ብልሽት እና የባለሥልጣናቱን ግድየለሽነት ፍንትው አድርጎ አሳይቷል።
ክልሉ በከፍተኛ የበጀት እጥረትና በልማት ጥማት ውስጥ ባለበት ወቅት፣ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በየመሥሪያ ቤቱ ካዝና ተከማችቶ መገኘቱና በቢሊዮኖች የሚቆጠር የሕዝብ ሀብት የት ገባ መባሉ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።
በካዝና የታጎረው በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ስንፍና ወይስ ስልታዊ ዝርፊያ?
የአገልግሎቱ ዋና ኃላፊ አቶ ታመነ ታምርሶ እንደገለጹት፣ በ49 የክልል ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በካዝና፣ በባንክና በተለያዩ ሂሳቦች ተከማችቶ የነበረ 249.7 ሚሊዮን ብር ጥቅም ላይ ሳይውል ተገኝቶ ወደ ማዕከላዊ ግምጃ ቤት መመለስ መግለፁን WT Media አረጋግጧል።
ይህ ገንዘብ ለታለመለት የልማት ሥራ ሳይውል “ተከማችቶ” መገኘቱ፣ አመራሩ የሕዝብን ችግር ለመፍታት ያለውን ዳተኝነት የሚያሳይ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ እንዲህ ያሉ በካዝና የሚቀመጡ ገንዘቦች ለስውር ምዝበራና ለወለድ ንግድ እንደሚውሉ የሚጠረጥሩ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፣ ድርጊቱ “ስልታዊ የሌብነት መንገድ” ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ።
የ1.4 ቢቢሊዮን ብር ማዳበሪያና የጥሬ ገንዘብ ጉድለት እንቆቅልሽ
ሪፖርቱ ካለፉት ዓመታት ጀምሮ ሲንከባለሉ የመጡ አሳሳቢ የኦዲት ግኝቶችን ይፋ አድርጓል።
ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ የአፈር ማዳበሪያ ኦዲት ግኝት መኖሩ ተገልጿል። አርሶ አደሩ ማዳበሪያ በውድ ዋጋ እየገዛና እጥረት ባለበት ክልል፣ እንዲህ ያለ ግዙፍ የገንዘብ ጉድለት መኖሩ የምግብ ዋስትናን አደጋ ላይ የሚጥል ወንጀል ነው።

ከ276 ሚሊዮን ብር በላይ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት አሁንም አልተመለሰም። ይህ የሚያሳየው በክልሉ የሕግ የበላይነት መላላቱንና የሕዝብን ሀብት የበሉ አካላት ያለ አንዳች ተጠያቂነት በሥልጣን ላይ መቆየታቸውን ነው።
የቦሎሶ ቦምቤው የሴፍትኔት ምዝበራ፥ ከድሃ ጉሮሮ መንጠቅ
የኦዲት ሪፖርቱ በዎላይታ ዞን ቦሎሶ ቦምቤ ወረዳ የተፈጸመውን ድፍረት የተሞላበት ስርቆት አጋልጧል።
በሴፍትኔት ፕሮግራም ለኩሬ ቁፋሮና ለውሃ መስመር ዝርጋታ ክፍያ ተፈጽሞ ስራው ግን አልተከናወነም።
ለንብ ቀፎ ግዥ የተመደበ በጀት ለታለመለት ዓላማ ሳይውል የቀረ ሲሆን ይህ ለዕለት ጉርሳቸው ለሚለፉ ደሃ አርሶ አደሮች የተመደበን ገንዘብ መዝረፍ፣ በክልሉ ያለው የሞራል ዝቅጠት ምን ያህል ጥልቀት እንዳለው ማሳያ ነው።
የምክር ቤቱ ዝምታ እና የኦዲት ሪፖርቱ መጋጨት
በዛሬው ዕለት የተጠናቀቀው የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ፣ እንደነዚህ ያሉ ግዙፍ የኦዲት ግኝቶችንና የምዝበራ ሪፖርቶችን አጀንዳ አድርጎ አለመወያየቱ አነጋጋሪ ሆኗል።
ምክር ቤቱ “ተቋማዊ የመፈጸምና የማስፈጸም አቅማችን ጨምሯል” በሚል ሪፖርት ሲያጸድቅ፣ የኦዲት አገልግሎቱ ግን በቢሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ ጉድለትና ያልተከናወኑ ፕሮጀክቶችን እያጋለጠ ነው።
አቶ ታመነ “የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓቱን እናጠናክራለን” ቢሉም፣ እስካሁን በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት ያጠፉ ባለሥልጣናት ላይ የተወሰደ ሕጋዊ እርምጃ አለመኖሩ፣ ሪፖርቱን “ለይስሙላ” ብቻ ያደርገዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝብ በመሠረተ ልማት እጦት፣ በስራ አጥነትና በድህነት እየማቀቀ ባለበት ወቅት፣ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በካዝና ታጉሮ መገኘቱና ቢሊዮኖች ደብዛቸው መጥፋቱ ታሪካዊ ክህደት ነው።
የኦዲት ግኝቶቹ በሪፖርት ብቻ መቅረት የለባቸውም፤ በቦሎሶ ቦምቤ፣ በጎፋና በሌሎች አካባቢዎች የተመዘበረው ሀብት ተመላሽ ተደርጎ ወንጀለኞች ለሕግ ሊቀርቡ ይገባል።
የክልሉ የውስጥ ኦዲት በባለሥልጣናት ጫና እንዳይደፈቅ፣ ገለልተኛ የፌዴራል ምርመራ እንዲደረግ እየጠየቅን ህብረተሰቡ ደግሞ የልማት በጀትንና የእርዳታ ሀብት የሚመዘብሩ አካላትን በንቃት እንድታጋልጡ ጥሪ እናቀርባለን።
ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media