የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 6ኛ መደበኛ ጉባኤውን በሹመቶችና ተጨማሪ በጀት በማጽደቅ ያጠናቀቀ ቢሆንም የቀጠለው የቢሊዮን ብር ምዝበራ፣ የባለሀብቶች እስርና ለሕዝብ ጥያቄዎች ትኩረት መንፈጉ ቅሬታ ማስነሳቱ ተገልጿል።

ይሁን እንጂ በዚሁ ከካቲት 06 እስከ 07/2018 ዓ.ም በተከሄደው ጉባኤው ላይ የቀረቡት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቶች እና የጸደቁት ተጨማሪ በጀቶች ከክልሉ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በእጅጉ የሚጋጩና የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄዎች ወደ ጎን ያገለሉ መሆናቸውን የኢኮኖሚ ባለሙያዎችና የፖለቲካ ተንታኞች ለ WT Media ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በስድስት ወራት ውስጥ ለ163 ሺህ 500 ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን በሪፖርታቸው ገልጸዋል። ሆኖም ይህ ቁጥር “የውሸት ሪፖርት ነው” የሚሉ ወገኖች በርካታ ናቸው።
ከ200 ሺህ በላይ ከዲፕሎማ በላይ የተማሩ ሥራ አጥ ወጣቶች ባሉበት በዎላይታ ዞን፣ ባለፉት ስድስት ወራት ምንም ዓይነት ተጨባጭ የሥራ ዕድል ባልተፈጠረበት ሁኔታ፣ ክልል አቀፍ ሪፖርቱ ይህን ያህል ቁጥር መጥቀሱ የሪፖርት ማጣፈጫ እንጂ በተግባር ያለ አይደለም ተብሏል።
“እነዚህ ዜጎች የት ነው ሥራ የተፈጠረላቸው?” የሚለው ጥያቄ ከሕዝቡ ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታ እየተነሳ ይገኛል።
ምክር ቤቱ ለ2018 በጀት ዓመት የሚውል ከ8.7 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት አጽድቋል። ሆኖም ለ WT Media አስተያየታቸውን የሰጡ የኢኮኖሚ ባለሙያ እንደሚሉት፦
ቀደም ሲል የተመደበው በጀት ለታለመለት ዓላማ ሳይውል፣ በኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና በተደራጀ ሌብነት መመዝበሩ በኦዲት ተረጋግጦ ባለበት ሁኔታ፣ የሕግ ተጠያቂነት ሳይረጋገጥ ተጨማሪ በጀት ማጽደቅ “ለተጨማሪ ምዝበራ በር መክፈት ነው” ብለዋል።
ከጋራ ግብር የሚሰበሰበው ገቢ በአመራሮች ትስስር ለዝርፊያ መጋለጡ፣ ጥቅም ያላቸው ባለሀብቶች ግብር እንዳይከፍሉ ሲደረግ፣ በአንጻሩ ከአመራሩ ጋር ያልተስማሙ ባለሀብቶች ላይ ከፍተኛ ጫና እየተደረገባቸው መሆኑ በክልሉ እየታየ ያለ አደገኛ አዝማሚያ ነው።
ጉባኤው በክልሉ እየተስተዋሉ ያሉ ታላላቅ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና የሙስና ወንጀሎችን ወደ ጎን ማለፉ “ሕዝብን መናቅ ነው” ተብሏል።
የዘይሴ ብሔረሰብ አባላት ሕገ-መንግሥታዊ የመብት ጥያቄዎችን በማንሳታቸው ብቻ፣ በተደራጀ ሁኔታ የዘር ማጥፋት ዘመቻ የሚመስል ጥቃትና ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው ቢሆንም ምክር ቤቱ በዚህ ላይ አልተወያየም።
በቁጫ ብሔረሰብ ላይ በማንነታቸው ምክንያት ብቻ እየደረሰ የሚገኘው ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና አስተዳደራዊ በደል በምክር ቤቱ አጀንዳነት ሳይነሳ አልፏል።
በጎፋ በኬንቾ ሻቻ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የተሰበሰበው ወደ አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በአመራሮች ተጭበርብሮ መበላቱና ይህን የጠየቁ ዜጎች መታሰራቸው የታወቀ ቢሆንም፣ ምክር ቤቱ ትኩረት አልሰጠውም።
በዎላይታ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማገልገል የሚማወቀው ኦቶና ሆስፒታል በድንገተኛ አደጋ ተቃጥሎ መልሶ ግንባታ ትኩረት ባለመሰጠቱ ምክንያት ተጓትቶ ሕዝቡ ለስቃይ ተዳርጎ እያለ የክልሉ መንግስት ቃል የገባውን አንደ መቶ ሚሊዮን ብር ባለመስጠቱ፣ ዩንቨርስቲውም ለመልሶ ግንባታ የገባውን አንድ መቶ ሚሊዮን ብር ባለመስጠትና እንደ ባለቤት ለጉዳዩ ፕረዚዳንቱ ትኩረት በመንፈጉ ምክንያት ህብረተሰቡ ለከፍተኛ ችግር መዳረጉን የምክር ቤት አባላት ያነሱ ቢሆንም በቂ ምላሽ አልተሰጠም።

በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች መልካም አስተዳደርን በሰላማዊ መንገድ የሚጠይቁ፣ ብልሹ አሠራርን የሚቃወሙ ግለሰቦች እና ባለሀብቶች ላይ የሚፈጸመው እስርና ማሳደድ በጉባኤው አልተገመገመም።
የኢንጅነር ብርሃነመስቀል ክንፌ ጉዳይ፦ ወጣቱ ባለሀብት በሕጋዊ መንገድ ኢንቨስት ለማድረግ ቢንቀሳቀስም፣ በአመራሮች ተከልክሎ ጉዳዩን በሕግ ለመፍታት በመሞከሩ ብቻ በሕገ-ወጥ መንገድ ታስሮ እንግልት እየደረሰበት ይገኛል።
በክልሉ መብታቸውን የሚጠይቁ ዜጎች ላይ የሚፈጸመው አስተዳደራዊ በደልና ማሳደድ፣ የክልሉን የሰላም ገጽታ እያበላሸው መሆኑ ተገልጿል።
ለ WT Media አስተያየታቸውን የሰጡ የፖለቲካ ተንታኞች እንደገለጹት፣ የሁለቱ ቀናት ጉባኤ መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎችን በውብ ቃላት ለመሸፈን የሞከረና ለዜጎች እሮሮ “ንቀት” ያሳየ ነው።
የዘይሴንና የቁጫን ሕዝብ ብሶት የዘነጋ፣ ሙስናን ያልታገለና የሥራ አጥ ወጣቶችን ቁጥር ያጋነነ ሪፖርት ያጸደቀው ምክር ቤት “የሕዝብ ድምፅ መሆኑ ቀርቶ የአመራሮች መከላከያ ምሽግ ሆኗል” ሲሉ ተችተዋል።
WT Media በክልሉ የሚታዩ የፍትሕ መጓደሎችንና የሀብት ምዝበራዎችን አድበስብሶ ለማለፍ የሚደረጉ ጥረቶችን በማጋለጥ ለሕዝብ ድምፅነቱን ይቀጥላል።
ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን!
Voice of Marginalized Community – WT Media