ግሎባል ፓራ-ዲፕሎማሲ (Global Para-Diplomacy) ለኢትዮጵያ ከተሞችና ዞኖች፣ በተለይም ለዎላይታ ዞን ልማትና ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ከፍተኛ ሚና ሊጫወት እንደሚችል ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ገለጹ።
እንደ የ WT Media ተጋባዥ ጸሐፊ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ገለጻ፣ ፓራ-ዲፕሎማሲ ማለት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዓይነት ሆኖ፤ የሚከናወነው በማዕከላዊ ወይም በፌደራል መንግስታት ደረጃ ሳይሆን በክልሎች፣ በዞኖች እና በከተሞች በኩል ነው።
ይህ ግንኙነት ከሙሉ እስከ ከፊል ነጻ በሆነ ሁኔታ የሚካሄድ ቢሆንም፣ በዋናነት እንደ ሀገራዊ የውጭ ግንኙነት ተቀጽላ ተደርጎ የሚወሰድ ዘርፍ ነው።
የፓራ-ዲፕሎማሲ ጥቅሞች ከእውቀት፣ ከባህልና ልምድ ልውውጥ ባሻገር ከቱሪዝም እና ከኢንቨስትመንት ዕድገት ጋር በጥብቅ የተሳሰሩ መሆናቸውን መጣጥፉ ያብራራል።
ዋና ዋና መገለጫዎቹም የእህትማማች ከተሞች ስምምነት መፈራረም፣ በተለያዩ ደረጃዎች የመግባቢያ ሰነዶችን (MOU) መፈረም፣ በዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና ማስተናገድ እንደሆነ ጠቅሷል።
በተጨማሪም የኢንቨስትመንት ልዑካንን መጋበዝና በዩኒቨርሲቲዎች መካከል የሚደረጉ ትብብሮችም ዋና ዋና መገለጫዎቹ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ከዓለም አቀፋዊነት (Globalization) ዕድገት ጋር ተያይዞ የፓራ-ዲፕሎማሲ ተመራጭነት እየጨመረ መጥቷል።
ይህም አካባቢያዊ ኃይሎች የዓለም አቀፍ ተጽዕኖአቸውን እንዲያሳድጉ ከማገዙም ባለፈ፣ በማዕከላዊ ቢሮክራሲ ዝርክርክነትና በቅልጥፍና ማነስ የሚፈጠሩ ክፍተቶችን በመድፈን ለሀገር ዕድገት አስተዋጽኦ ያበረክታል።
የWT Media ተጋባዥ ጸሐፊ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ አክለውም፣ ዎላይታ ዞን እንደ ዞን ያሉበትን ተጨባጭ ችግሮች መነሻ በማድረግ ይህንኑ የዲፕሎማሲ መንገድ በመጠቀም ችግሮቹን መፍታት እንደሚችል አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት የውጭ ግንኙነት ስልጣን ለፌደራል መንግስት የተሰጠ ቢሆንም፣ በተግባር ግን በፌደራሉ ይሁንታ የሚከናወኑ የድንበር ተሻጋሪ (Transborder) ግንኙነቶች ይስተዋላሉ።
ለምሳሌ፦ የሶማሌ ክልል ከሶማሊያ አካባቢያዊ መንግስት አካላት ጋር ያለው ግንኙነት፥ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከኬንያ ጋር የሚያደርገው ግንኙነት ተጠቅሷል።
ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ የሕግ ክፍተት ያለ ስለሚመስል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ፕሮፌሰሩ አሳስበዋል።
በፌደራል መንግስትና በትግራይ መካከል የነበረው አለመግባባት እንዲሁም አሁን በትግራይ በኩል ከኤርትራ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት የመፍጠር ፍላጎት በቸልታ መታየት እንደሌለበት በመጠቆም፣ የውጭ ግንኙነቱ የሕግ፣ የሞራልና የፖለቲካ ችግር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ቻይና ከ1970ዎቹ ጀምሮ በከተሞቿና በግዛቶቿ በኩል ከ2,500 በላይ ስምምነቶችን በማድረጓ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቷን ማሳደግ ችላለች። ዩኒቨርሲቲዎቿም የዚህ ስኬት ተጠቃሚ ሆነዋል።
በማጠቃለያው፣ የዎላይታ ዞን፣ የዎላይታ ሶዶ ከተማ እና የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በተናጠልም ሆነ በቅንጅት ከፓራ-ዲፕሎማሲ ተጠቃሚ ለመሆን መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና አሳስበዋል።
አዲስ አበባ ከተማም ከደቡብ አሜሪካዋ ሳኦ ፓውሎ (Sao Paulo) ሰፊ ተሞክሮ መቅሰም እንዳለባት ጠቁመዋል።
ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media