GridArt_20260216_180259639

በደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ ለአንድ ክፍለ ዘመን ያህል የዎላይታንና የአጎራባች አካባቢዎችን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ነፍስ ሲታደግ የቆየው የኦቶና ሆስፒታል፣ “ምክንያቱ ባልታወቀ” የእሳት አደጋ ከወደመ በኋላ መልሶ የመገንባቱ ሂደት በባለሥልጣናት ቸልተኝነት መገታቱ ሳያንስ፣ አሁን ደግሞ የሕክምና ኮሌጁን የመዝጋትና የጤና ቱሪዝም የማሸሽ አሳፋሪ ውሳኔ መተላለፉ ተጋልጧል።

ይህም በዎላይታ የጤናና የትምህርት ተቋማት ላይ የታቀደ “ታሪካዊ ውድቀት” ለማድረስ የሚደረግ ድብቅ ፖለቲካዊ ሴራ መሆኑ ተመልክቷል።

ኦቶና ሆስፒታል እሳት አደጋ በተነሳበት ቀን ለመቆጣጠር ከአከባቢው የተሰበሰበው ህዝብ

የኦቶና ሆስፒታል ከወደመ ወራት ቢቆጠሩም፣ መልሶ ግንባታው እንዳይጀመር ዋነኛ እንቅፋት የሆኑት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕሬዝደንት አቶ ጥላሁን ከበደ እና የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ጉቼ ጉሌ መሆናቸውን WT Media ያሰባሰበው መረጃ ያረጋግጣል።

ለመልሶ ግንባታው የተከፈተው አካውንት ፈራሚዎች እነዚህ ሁለት ባለሥልጣናት ቢሆኑም፣ ክልሉና ዩኒቨርሲቲው ቃል የገቡትን ገንዘብ እስካሁን ገቢ አላደረጉም። በተከፈተው አካውንቱ ገብቶ አሁን ቀረ የተባለው 13.1 ሚሊዮን ብርም ቢሆን ከሌሎች ግለሰቦችና ተቋማት የተሰበሰበ ነው።

ይህ ቸልተኝነት በጤና መድህን ተጠቃሚ የሆኑ አነስተኛ ገቢ ያላቸው አርሶ አደሮች የግል ሕክምና ተቋማት ለሚጠይቁት ከፍተኛ ክፍያ ተጋልጠው ሕይወታቸው እንዲያልፍ ምክንያት እየሆነ ይገኛል።

ከሆስፒታሉ መውደም በስተጀርባ ያለውን ድብቅ ዓላማ ይበልጥ ግልጽ የሚያደርገው፣ በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሴነት ተላለፈ የተባለው ውሳኔ ነው።

ከ100 ዓመታት በላይ ሲያገለግል የነበረውና እስከ ድህረ-ምረቃ (Post-graduate) ስፔሻላይዜሽን ትምህርት ሲሰጥ የነበረው የጤና ሳይንስና ሕክምና ኮሌጅ፣ ከልህቀት ማዕከልነት እንዲወጣና እንዲዘጋ ተወስኗል።

ለሕክምና ትምህርት ልህቀት ማዕከልነት (Undergraduate) የአርባምንጭና የዲላ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲመረጡ መደረጉ፣ በዎላይታ ላይ የተከፈተውን ስልታዊ የልማት አፈና የሚያረጋግጥ እንደሆነ የአከባቢው ምሁራን ቅሬታ እያቀረቡ ይገኛሉ።

ታማኝ ምንጮች ለ WT Media እንደገለጹት፣ የኦቶና ሆስፒታል ተጠግኖ አገልግሎት እንዳይሰጥ መደረጉ ሁለት ዋና ዓላማዎች አሉት፦

ወደ ዎላይታ ሶዶ የሚመጣውን ሰፊ የሕክምና ፈላጊ ፍሰት ወደ ሌላ አካባቢ ለማዞር ታስቦ የተደረገና ታሪካዊው ሆስፒታልና ኮሌጁ እንዲጠፉ በማድረግ የአካባቢውን የማኅበራዊ አገልግሎት አቅም ማዳከም ነው ተብሏል።

ሆስፒታሉ በምን ምክንያት እንደተቃጠለ ለሕዝብ የተሰጠ ግልጽ መግለጫ የለም።

ኦቶና ሆስፒታል ከቃጠሎ በኃላ

ለመልሶ ግንባታ ከተለያዩ አካላት የተሰበሰበው ጠቅላላ ሀብትና ገንዘብ ኦዲት ተደርጎ ለሕዝብ ይፋ አልተደረገም።

የአካባቢው አመራሮች ለዚህ በሚሊዮኖች ሕይወት ላይ ለተጋረጠ አደጋ የሰጡት ትኩረት “ዜሮ” መሆኑ ታዝቧል።

የኦቶና ሆስፒታል መውደም የአንድ ተቋም መጥፋት ብቻ ሳይሆን፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዎላይታና የአጎራባች ሕዝቦች የሕይወት ዋስትና መነጠቅ ነው።

ይህንን ታሪካዊ ሆስፒታልና የሕክምና ኮሌጅ ለመዝጋት የሚደረገው “ድብቅ ፖለቲካዊ ሴራ” በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል።

በመሆኑም የፌዴራል መንግሥት የኦቶና ሆስፒታል ቃጠሎ መንስኤ በገለልተኛ አካል እንዲመረመርና የሕክምና ኮሌጁን የመዝጋት ውሳኔ እንዲታገድ በርካቶች እየጠየቁ ይገኛሉ።

በተጨማሪም “ይህ ተቋም የሁላችንም ኩራትና የሕይወት መሠረት በመሆኑ፣ ተቋሙን ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚደረገውን ትግል አጠናክረን እንቀጥል” የሚል ጥሪ ቀርቧል።

ለክልሉና ለዩኒቨርሲቲው አመራሮች፦ የታሪካዊ ተጠያቂነትና የሕዝብ ርግማን ሳይቀድማችሁ፣ ቃል የገባችሁትን በጀት ገቢ በማድረግ ግንባታውን በአስቸኳይ ጀምሩ! ጥሪ ከተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች እየተሰማ ይገኛል።

ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media