በዎላይታ 81 ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል ተገኘ፤ የምስራች ወይስ የብዝበዛ ስጋት?

በዎላይታ 81 ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል ተገኘ፤ የምስራች ወይስ የብዝበዛ ስጋት?

በዎላይታ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች፣ ለኢንዱስትሪ ቦይለሮችና ለጡብ ማምረቻ እጅግ ተመራጭ የሆነ 81 ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል መገኘቱ ቢገለፅም ከወዲሁ አነጋጋሪ ጥያቄዎች ለምን ይነሳሉ ?

የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት በዎላይታ ዞን ኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ ውስጥ 81 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍንና 81 ሚሊዮን ቶን የሚመዝን የድንጋይ ከሰል ክምችት በጥናት መገኘቱን በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።

ይህ ግኝት ለሀገሪቱ የኢነርጂ ዘርፍ ትልቅ ተስፋ ቢሆንም፣ በአካባቢው ነዋሪዎችና በወጣቶች ዘንድ ግን “የሀብቱ ባለቤት ማነው?” የሚለው ጥያቄ በከፍተኛ ሁኔታ እየተነሳ ይገኛል።

እንደ ኢንስቲትዩቱ መረጃ፣ የተገኘው የድንጋይ ከሰል አይነት (Sub-bituminous to high volatile) ሲሆን፣ አነስተኛ የሰልፈር መጠን ያለው በመሆኑ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች፣ ለኢንዱስትሪ ቦይለሮችና ለጡብ ማምረቻ እጅግ ተመራጭ ነው።

ኢትዮጵያ ለድንጋይ ከሰል ግዢ በዓመት የምታወጣውን ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለመታደግ ይህ ግኝት ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል።

ይህ ግኝት ይፋ በሆነበት በዚህ ወቅት በዎላይታ ዞን ከ200 ሺህ በላይ ከዲፕሎማ በላይ የተማሩ ወጣቶች ስራ አጥ ሆነው እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

WT Media ቀደም ሲል በቦሮዳ ወረዳ የድንጋይ ከሰል ማምረት የጀመሩ ባለሀብቶችና የጥቅም ተጋሪ አመራሮች ሀብቱን በህገ-ወጥ መንገድ እየበዘበዙት እንደሚገኙ፣ ለአካባቢው ወጣቶች ግን የተረፈው ስራ አጥነትና የአካባቢ መራቆት ብቻ እንደሆነ መዘገቡ ይታወሳል።

አሁንም በኪንዶ ዲዳዬ የተገኘው ይህ ግዙፍ ሀብት እንደ ቦሮዳው “በጥቂቶች የሚመዘበር” ወይስ “የአካባቢውን ወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥር?” የሚለው ጉዳይ አሳሳቢ ሆኗል።

ዎላይታ ኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ የጊቤ 3 (Gibe III) የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ  የሚገኝበት ስፍራ ነው።

ኢትዮጵያ ከዚህ ማመንጫ ለጎረቤት ሀገራት ኤሌክትሪክ በመሸጥ በዓመት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ብታገኝም፣፣ የማመንጫው ባለቤት የሆነው የዲዳዬ ሆነ አብዛኛው የዞኑ ህዝብ ግን አሁንም በጨለማ ውስጥ ይገኛል።

መሰረታዊ ልማቶች ያልተሟሉበትና በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች ተጀምረው በቆሙበት በዚህ ወቅት፣ አዲስ የተገኘው የድንጋይ ከሰል ክምችት ለአካባቢው ህዝብ የኑሮ መሻሻል ያመጣል ወይስ ተጨማሪ የመልካም አስተዳደር እክል? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።

የማዕድን ሀብት መገኘት ለሀገር ዕድገት ፋይዳው የላቀ ቢሆንም፣ የአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ካልተረጋገጠ ግን ግጭትንና ብዝበዛን ከመጋበዝ ባለፈ ፋይዳው አነስተኛ ነው።

የፌዴራልና የክልል መንግስታት ይህንን ግኝት ወደ ተግባር ሲቀይሩ፦ ለሰለጠኑት ስራ አጥ ወጣቶች ቅድሚያ የሥራ ዕድል መስጠት፤ ህገ-ወጥ የጥቅም ትስስርን መከላከል፤ ከሀብቱ የሚገኘውን ገቢ ለአካባቢው መሰረተ ልማት (መብራትና መንገድ) ማዋል ይገባቸዋል።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media