በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በቡርጂ ዞን የሚገኙ እናቶች እና ሕፃናት በመንግስት ቸልተኝነት እና በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ለከፋ ስቃይ እና ለሞት እየተዳረጉ መሆኑን ለWT Media የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
አካባቢው ለዘመናት በዘለቀ የመንገድ እና የድልድይ መሰረተ ልማት እጦት ሳቢያ ሲሰቃይ የቆየ፣ አሁን ደግሞ ያለው ጥቂት የአምቡላንስ አገልግሎት ለግል ጥቅም መዋል እና ለቢዝነስ መከፈቱ ችግሩን ወደ ማይመለስ አደጋ ቀይሮታል ይላሉ የአከባቢው ነዋሪዎች ለ WT Media።


አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም በዞኑ የአምቡላንስ አገልግሎት ለማግኘት የሚገደዱ ወላድ እናቶች የነዳጅ ወጪ እና የሾፌር ውሎ አበል ከኪሳቸው እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ ይላሉ።
ይህንን ማድረግ የማይችሉ እናቶች አነስኛ ገንዘብ በመከፍል ባለሁለት እግር ሞተር ሳይክል ወይም በእንጨት ቃሬዛ ተጭነው ረጅም ኪሎ ሜትሮችን እንዲጓዙ ይገደዳሉ፤ በዚህም ምክንያት በርካታ እናቶች በጉዞ ላይ ህይወታቸው ያልፋል።
ለWT Media የደረሱ ምስሎች እንደሚያሳዩት፣ በህክምና እጦት ህይወታቸው ያለፈ ህፃናት አስከሬን በካርቶን ተጭኖ በሞተር ሳይክል ለቀብር ሲወሰድ ይታያል።

ይህ ክስተት በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ ስነ-ልቦናዊ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።


WT Media በዚህ አሳሳቢ ጉዳይ ዙሪያ ምላሽ ለማግኘት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ እና የቡርጂ ዞን ተወላጅ የሆኑትን አቶ እንዳሻው ሽብሩን በተደጋጋሚ ለማነጋገር ሙከራ ቢያደርግም፣ ግለሰቡ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሳይሳካ ቀርቷል።
ከአምቡላንስ ችግሩ በተጨማሪ፣ በዞኑ የሰገን ወንዝ ላይ ድልድይ ባለመኖሩ ህዝቡ በራሱ አቅም የእንጨት ድልድይ ለመስራት እየታገለ ይገኛል።

ቀደም ሲል WT Media እንደተዘገበው፣ በዞኑ የሰገን ወንዝ ድልድይ ባለመኖሩ ህዝቡ በእንጨት ድልድይ ለመሻገር ሲገደድ መቆየቱ ይታወሳል።
ይህ የመንገድ ችግር ከአምቡላንስ እጥረት ጋር ተዳምሮ እናቶች በሞተር ሳይክል ወይም በእንጨት ቃሬዛ ተሸክመው ረጅም ኪሎ ሜትሮችን እንዲጓዙ እና መንገድ ላይ የእናቶች፣ የህፃናትና ሌሎች ወገኖች ህይወት እንደ ቅጠል እንዲረግፍ ምክንያት ሆኗል።


“የወላድ እናቶችን አስክሬን በቃሬዛ፣ የህፃናትን አስከሬን በካርቶን ይዘን የምንመለስበት ጊዜ መቼ ያበቃል?” የሚለው የቡርጂ ህዝብ ጥያቄ፣ አሁንም ከክልል እስከ ፌዴራል ያሉ የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡት ይጠይቃል።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media
2 thoughts on ““አመራሮች ለጤና አገልግሎት የተመደበውን አምቡላንስ ለሽርሽር፥ የመንገድ ችግር ጥያቄያችንን ችላ ብለው የወላድ እናቶችን አስክሬን በቃሬዛ፣ የህፃናትን አስከሬን በካርቶን ይዘን የምንመለስበት ጊዜ መቼ ያበቃል?” – የቡርጂ ህዝብ”
Comments are closed.