GridArt_20260302_180600766

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መዲና፣ በዎላይታ ሶዶ ከተማ ለዓመታት የተጓተተው የመንገድ ግንባታ ዛሬ ለሦስት ታዳጊ ሕፃናት ሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑን ለ WT Media ከስፍራው የደረሰ መረጃ ያመለክታል።

ዛሬ የካቲት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጧት በከተማዋ በጣለው ድንገተኛ ዝናብ ምክንያት፣ በመርካቶ ወፍጮ ሰፈር አካባቢ ለግንባታ ተቆፍሮ ክፍት በሆነ “ዲች” (የፍሳሽ ቦይ) ውስጥ ተኝተው የነበሩ አራት የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናት በጎርፍ ተወስደዋል።

ከነዚህ አራት ሕፃናት መካከል ሦስቱ ወዲያውኑ ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ አንዱ ሕፃን ተርፎ ለሕክምና ወደ ጤና ተቋም መወሰዱን WT Media ከታማኝ የመረጃ ምንጮች አረጋግጧል።

WT Media ስለ አደጋው ዝርዝር ሁኔታና ስለ ሟቾቹ ማንነት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ ከተማው ፖሊስ ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

ይህ አሳዛኝ አደጋ የደረሰው በከተማዋ የተጀመሩ የመንገድ ግንባታዎች በተለያዩ ሰበቦች ሳይጠናቀቁ ለዓመታት በመቆየታቸውና ለሕዝብ ደኅንነት አስጊ በሆነ ሁኔታ ክፍት ሆነው በመተዋቸው ነው።

ነዋሪዎች “የአመራሮች ቸልተኝነትና የፕሮጀክቶች መጓተት ዛሬ የሕፃናትን ሕይወት በልቷል” ሲሉ ከፍተኛ ምሬታቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።

WT Media በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ሕፃናት ጥልቅ ሐዘኑን ይገልጻል።