GridArt_20260227_211325582

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጎፋ ዞን ከንቾ ሻቻ ጎዝዲ በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ዜጎች ከተሰበሰበው ወደ አንድ ቢሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ውስጥ፣ ከወራት በፊት ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ በቼክ ሊያወጡ ሲሉ የተያዙት አቶ መሐመድ ኑርሁሰን ሲራጅ፤ በማረሚያ ቤት ውስጥ ከፍተኛ ድብደባና ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ለፍርድ ቤት በለቅሶ ገልጸዋል።

በዛሬው ዕለት፣ የካቲት 20 ቀን 2018 ዓ.ም በጎፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡት ተጠርጣሪው አቶ መሐመድ ኑር፤ በሳውላ ማረሚያ ቤት ውስጥ የሚደርስባቸውን ስቃይ ለችሎቱ ይፋ ማድረጉን በቦታው የተገኘ የ WT Media መረጃ ምንጭ አስረድተዋል።

በዚሁ ችሎት፣ “ድንገት ልገደል ስለሚችል የኢትዮጵያ ሕዝብ ይወቅልኝ” ያሉት አቶ መሐመድ፤ እስካሁን ድረስ በአንድ ጨለማ ክፍል ውስጥ ብቻቸውን ተዘግቶባቸው እንደሚቆዩና ለፍርድ ቤት ሲባሉ ብቻ ዛሬ ወደ ውጭ መውጣታቸውን በእንባ ታጅበው ተናግረዋል።

አቶ መሐመድ ለፍርድ ቤቱ እንደገለጹት፣ ወንጀሉን ከዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳግማዊ አየለ ጋር በጋራ መሥራታቸውን ለመርማሪዎች ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ሆኖም ይህንን ቃላቸውን እንዲክዱና “በሰዎች ተነሳስቼ ነው የአቶ ዳግማዊን ስም የጠራሁት” ብለው እንዲናገሩ የዞኑ አቃቤ ሕግ መምሪያ በተደጋጋሚ በማረሚያ ቤት ድረስ እየመጣ እንዳስጠነቀቃቸው ገልጸዋል።

ይህንን ትዕዛዝ ባለመቀበላቸውም ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባቸውና ሰብዓዊ ክብራቸው እንደተጣሰ አስረድተዋል።

WT Media ቀደም ሲል በዘገበው መሠረት፣ በዚህ የእርዳታ ገንዘብ ዝርፊያ ዙሪያ ከ20 በላይ ሰዎች ታስረው የነበረ ቢሆንም፣ ዋናው የዝርፊያ ጉዳይ ግን እስካሁን እልባት አላገኘም።

ታስረው በዋስትና የተፈቱ ግለሰቦች ቢኖሩም፣ መዝገባቸው ባለመዘጋቱና ንብረቶቻቸው (ስልክና ኮምፒውተር) ባለመመለሳቸው አሁንም በማስፈራሪያ ውስጥ ይገኛሉ።

በዚህ ጉዳይ ታስረው በዋስ የተፈቱ የፖሊስ አባላትና አቃቤ ሕግም ወደ ሥራቸው እንዳይመለሱ ተደርገዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ የሕዝብን ሀብት የዘረፉ አመራሮችን ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ፣ ጉዳዩን ለመሸፈንና ምስክሮችን በማሳደድ ላይ መጠመዳቸውን WT Media በተደጋጋሚ ሲዘግብ ቆይቷል።

ተጠርጣሪው በአደባባይ “ልገደል እችላለሁ” ብለው መጮኻቸው፣ በጎፋ ዞን ያለው የፍትሕ ሥርዓት በባለሥልጣናት ተጽዕኖ ሥር መውደቁንና የተጎጂዎች ደም ለባለሥልጣናት መክበሪያ እየዋለ መሆኑን ያሳያል።

በንጹሐን ዜጎች ደም ላይ የቆመው ይህ ግዙፍ ዝርፊያና የተጀመረው የምስክሮች አፈና በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል።

የፌዴራል መንግሥትና የሰብዓዊ መብት ተቋማት በአቶ መሐመድ ኑር ላይ እየደረሰ ያለውን ድብደባ እንዲያቆሙና የአቶ ዳግማዊ አየለ አስተዳደር በዚህ ዝርፊያ ላይ የተሳተፉ አካላት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ በገለልተኛ አካል እንዲመረመር WT Media ጥሪውን ያቀርባል።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media