GridArt_20260303_171936717

ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ በዎላይታ ህዝብ ዘንድ እጅግ የሚከበሩትና የአገር ባለውለታ የሆኑት ባለታሪኩ አባት አባባ ዳቼ ታንቱ፣ በ107 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸው ተሰምቷል።

አባባ ዳቼ ባጋጠማቸው የጤና እክል በሕክምና ሲረዱ ቆይተው፣ ባለፈው እሁድ የካቲት 22 ቀን 2018 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን WT Media ከቤተሰቦቻቸው ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

አባባ ዳቼ ታንቱ በዎላይታ አውራጃ፣ በአበላ አባያ ወረዳ በ1912 ዓ.ም ተወልደው ያደጉ ሲሆን፤ የአካባቢያቸውን መሬትና ህዝብ ከወራሪዎች በጀግንነት በመከላከል የሚታወቁ አንጋፋ አባት ነበሩ።

 በተለይም “የአባቶቻችንን መሬት ለወራሪዎች አሳልፈን አንሰጥም” በማለት ነፍሳቸውን አስይዘው የታገሉና የአባያ መሬት ዛሬ ላለበት ክብር እንዲበቃ የራሳቸውን ታሪካዊ አሻራ ያሳረፉ ጀግና ናቸው።

 አባባ ዳቼ የቀድሞ የሁምቦ ወረዳ አስተዳዳሪ የዶክተር ዳንኤል ዳቼ አባትም ነበሩ። አባባ ዳቼ ታንቱ በቁሳዊው ዓለም ለሀገራቸው ካደረጉት ተጋድሎ ባሻገር፣ በመንፈሳዊው ዘርፍም ቀዳሚ እንደነበሩ WT Media ከቤተሰቦቻቸው ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በ1948 ዓ.ም በአበላ አባያ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ ጌታን እንደ ግል አዳኝ አድርገው ከተቀበሉ ጥቂት ክርስቲያኖች አንዱ ነበሩ።

 በዚያው ወቅት የመሠረቱት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመሪ ሽማግሌነት እስከ እርጅና ዘመናቸው ድረስ በታማኝነት ያገለገሉ ሲሆን፣ በብዙዎች ዘንድ “የወንጌል አርበኛ” በመባል ይጠራሉ።

እኚህ ታላቅ አባት ረጅምና የተባረከ ዕድሜን አሳልፈው ሲያልፉ፣ ለቁጥር የሚያዳግት ትልቅ ትውልድ አፍርተዋል። 

አባባ ዳቼ፦ የ7 ልጆች አባት፤ የ60 የልጅ ልጆች፤ የ63 የልጅ ልጅ ልጆች እና የ4 የልጅ ልጅ ልጅ ልጆች ባለቤት ነበሩ።

በአጠቃላይ 134 የሚሆኑ ተተኪ ትውልዶችን የማየት በረከትን አግኝተዋል።

ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ (WT Media) ለታላቁ አባት ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲሁም ለአበላ አባያ ህዝብ በሙሉ መጽናናትን ይመኛል።

የአባባ ዳቼ ታንቱ ነፍስ በሰላም ትረፍ!

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media