የዎላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር የተጓተተ መንገድ ግንባታ በፈጠረው ጎርፍ ስለደረሰው የሰው ህይወት መጥፋት አደጋ ዝምታን በመምረጥ “የመንገድ ግምገማ” ማካሄዱ በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ መፍጠሩ ተገልጿል።
በደቡብ ኢትዮጵያ መዲና፣ በዎላይታ ሶዶ ከተማ በመንገድ ግንባታ መጓተት ምክንያት የሦስት ሕፃናትና የአንዲት እናት ሕይወት በጎርፍ መጥፋቱን ተከትሎ፣ የከተማው አስተዳደር በዛሬው ዕለት በመንገድ ግንባታው ዙሪያ ግምገማ ማካሄዱን አስታውቋል።



ሆኖም አስተዳደሩ በሰጠው መግለጫ ስለጠፋው የሰው ሕይወት የገለጸው ሐዘንና የሰጠው ይፋዊ ምላሽ የለም።
የዎላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ዛሬ ባወጣው መረጃ መሠረት፣ ከንቲባ ወ/ሮ እታገኝ ኃይለማርያም ከኮካቴ እስከ ግብርና ኮሌጅ እየተሠራ ያለውን የአስፋልት መንገድ ግንባታ ከአማካሪ ድርጅቶችና ከኮንትራክተሩ ጋር ገምግመዋል።
ግንባታው የአየር ሁኔታ ሳይገድበው በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቅ እንዳለበት ከንቲባዋ አሳስበዋል።
ከንቲባዋ በምልከታቸው ወቅት ነዋሪዎች በጎርፍና በጭቃ እየተቸገሩ መሆኑን ጠቅሰው ግንባታው ትኩረት እንዲሰጠው ገልጸዋል። ሥራው “ሰው ተኮር” እና የደኅንነት ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን አጽንኦት ሰጥተዋል።
WT Media ትናንት በመርካቶ ወፍጮ ሰፈር አካባቢ በመንገድ መጓተትና በዲች መቆፈር ምክንያት ሦስት ሕፃናትና አንዲት እናት በጎርፍ ተወስደው ሕይወታቸው ማለፉን መዘገቡ ይታወሳል።
ሆኖም ከተማ አስተዳደሩ ዘገባችንን ተከትሎ ዛሬ ባካሄደው የግምገማ መድረክ ላይ በአደጋው ሕይወታቸው ስለጠፋው ወገኖች የገለጸው ምንም ዓይነት ሐዘን የለም፤ WT Media ያወጣውን የሞት አደጋ ዘገባ እስካሁን አላስተባበለም።
የዜጎች ሕይወት በቸልተኝነት በተቆፈሩ ጉድጓዶች እየጠፋ ባለበት ወቅት፣ አስተዳደሩ ስለ “ግምገማ” ብቻ መግለጫ መስጠቱ በነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥሯል።
የከተማው ዋና የመንግሥት ተጠሪ ረዳት ፕሮፌሰር ዘገየ ጳውሎስ ከተማ መንግሥት ግንባታውን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን ቢገልጹም፣ በተግባር ግን ክፍት የሆኑ የፍሳሽ ቦዮች ለዜጎች ሞት ምክንያት እየሆኑ ይገኛሉ።
ግንባታው ከኮካቴ እስከ ያዕቆብ ሆቴል ያለውን የጎርፍ ችግር በዘላቂነት ይፈታል ቢባልም፣ አሁን ባለው ፍጥነት ግን የዝናብ ወቅት መግባቱን ተከትሎ ተጨማሪ አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ነዋሪዎች ይሰጋሉ።
WT Media የዜጎችን ሕይወት የቀጠፈውን ይህንን የግንባታ መጓተትና የአስተዳደሩን ምላሽ ተከታትሎ መዘገቡን ይቀጥላል።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media