በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ሶዶ ከተማ፣ በመርካቶ ክፍለ ከተማ ፋና ወምባ ቀበሌ ውስጥ፣ አመራሮች ከባለሀብት ጋር በመመሳጠር ሕጋዊ ይዞታዎችን ያለ አንዳች የጽሑፍ ትእዛዝ እያፈረሱና ባለይዞታዎችን እያሳሰሩ መሆኑን WT Media የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
ባለይዞታ የሆነውና በሊስትሮ ስራ የሚተዳደር ተበዳዩ ወጣት ተካልኝ ኤርሚያስ ለሚዲያችን በላከው አሳዛኝ በተጨባጭ ሰነድ በተደገፈ ምስክርነት፣ ቤታቸው ፈርሶ ንብረታቸው በጭነት መኪና ተጭኖ የት እንደደረሰ እንደማያውቁ በለቅሶ ገልጸዋል።
እንደ ተበዳዩ ገለጻ፣ ይዞታውን በመውሰድ ማስፋፊያ እንዲሰጠው የጠየቀው አንድ ባለሀብት ሲሆን፣ ለዚህም ፈጻሚ የሆኑት ግብረ-አበሮቹ ደግሞ ከከፍተኛ አመራር በስልክ ትዕዛዝ የተቀበሉ የተባለላቸው የመርካቶ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ኃላፊ፣ የፋና ወምባ ቀበሌ አስተዳደር ኃላፊ ናቸው ብሏል።
እነዚህ አመራሮች የፋና ወምባ ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ “ይዞታው ሕጋዊ ነው፣ አታፍርሱ እኔ እጣራለሁ” እያለ፣ የቃለ-ጉባኤ ውሳኔና ከበላይ አካል የተሰጠ ደብዳቤ ሳይኖር፣ “ትእዛዝ አለኝ” በሚል ብቻ ግብረ-ኃይል አሰማርተው ቤቱን ማፍረሳቸው ታውቋል።
ተበዳዩ ወጣት ነባር የባለይዞታ ልጅ ሲሆን፣ ቤቱን የሠራው በአባቱ ሕጋዊ ይዞታ ላይ በካቢኔ ውሳኔ መሠረት መሆኑን WT Media የተመለከተው ሰነዶች ያሳያሉ።

የሰነድ መረጃ እንደሚያመለክተው ቤቱ በህጋዊ ካሪኒ ተቆርጦ የተሰራው ነሐሴ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ነበር።
ቤቱ ሲፈርስ ባለይዞታው እንዲታሰር የተደረገ ሲሆን፣ ከፈረሰው ቤት ላይ የወጣው ቆርቆሮና እንጨት በጭነት መኪና ተጭኖ የት እንደደረሰ እስካሁን አይታወቅም።
በአካባቢው የሚሰሙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ የቀበሌውና የክፍለ ከተማው አመራሮች ይህንን ድፍረት ያገኙት “ከጀርባችን የከተማው ከፍተኛ አመራሮች እጅ አለበት” በሚል መተማመኛ ነው።
የማፍረስና የማጣራት ሥልጣን የማዘጋጃ ቤት ሆኖ ሳለ፣ የቀበሌ አመራሮች በራሳቸው ጊዜ ግብረ-ኃይል አምጥተው ማፍረሳቸው በግልጽ የአስተዳደራዊ ወረራ መሆኑን ያሳያል።
በንጹሐን ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ይህ ዓይነቱ አፈናና የንብረት ዝርፊያ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል።
WT Media በዎላይታ ሶዶ ከተማ ከፍተኛ አመራሮች በከተማዋ ከባለሀብቶች ጋር በመመሳጠር እየዘረፉ የሚገኙትን በቀጣይ በዝርዝር ማቅረቡ እንደተጠበቀ ሆኖ የዚህን በሊስትሮ እየሰራ በአባቱ ይዞታ የሰራሁን ህጋዊ ቤት ካሰሩ በኃላ ከባለሀብት ጋር ተመሳጥረው አፍርሰው ስላፈናቀሉት ወጣት ጉዳይ በቅርበት እየተከታተለ ለሚመለከታቸው የፍትሕ አካላት ጥያቄውን ማቅረቡን ይቀጥላል።
የከተማው አስተዳደርና የፍትሕ አካላት በእነዚህ አመራሮችና በባለሀብቱ ላይ አስቸኳይ ምርመራ በማድረግ ለተበዳዩ ፍትሕ እንዲሰጡ እንጠይቃለን።
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media