GridArt_20260304_211313891

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በቡርጂ ዞን ሶያማ ዙሪያ ወረዳ የሚገኙ አራት ቀበሌዎች (በኖ፣ ምስሞ፣ አራሻ እና ቦንጮ) ከባድ የመሠረተ ልማት ችግር እና የመንግስት ትኩረት ማነስ ክፉኛ እንዳማረራቸው ገልጿል።

ነዋሪዎቹ የሚያቀርቧቸው የልማት ጥያቄዎች ከአስተዳደሩ ሆነ ከክልሉ ተገቢውን ምላሽ ባለማግኘታቸው በአካባቢው ላይ ከፍተኛ ቁጣ እየቀሰቀሰ እንደሚገኝ ለ WT Media ተናግረዋል።

በአካባቢው የሚገኘው የባጋደ ድልድይ ምንም ዓይነት ሙያዊ ጥናትና ኢንጂነሪንግ ዲዛይን ሳይደረግለት የተገነባ እንደሆነ ተገልጿል።

መንግስት ለግንባታው ቸልተኝነት ማሳየቱ ድልድዩን ለከፍተኛ አደጋ ተጋላጭ አድርጎታል።

ይህ ድልድይ በማህበረሰቡ ላይ ድንገተኛ አደጋ ሊያደርስ እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎች የመንግስት ያለህ እያሉ ይገኛሉ።

በአካባቢው ያለው የመንገድ ችግር የወላድ እናቶችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሏል።

ምጥ የያዛቸው እናቶች የጤና ተቋም ለማግኘት በዘመናዊ አምቡላንስ ፋንታ በቃሬዛ ተሸክመው ወደ ጉማይዴ ለመውሰድ እንደሚገደዱ ተገልጿል።

ይህ አሳዛኝ ሁኔታ እናቶችን ለከፍተኛ እንግልትና ለሞት አደጋ እያጋለጠ ሲሆን የዞኑ አስተዳደር ግን ለጉዳዩ ጆሮ ዳባ ማለቱ ተጠቁሟል።

የበኖ፣ ምስሞ፣ አራሻ እና ቦንጮ ነዋሪዎች ለቀረቧቸው መሠረታዊ የልማት ጥያቄዎች ከዞኑ አመራሮች የተሰጠው ምላሽ “ያልተገባ ጥያቄ” የሚል መሆኑ ቅሬታውን ይበልጥ አባብሶታል።

ነዋሪዎቹ ይህንን ምላሽ የመልካም አስተዳደር እጦት እና የሕዝብን ድምጽ የመናቅ ተግባር አድርገውታል።

ይህ ችግር በቡርጂ ዞን ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ በአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የሚታየው ፍትሃዊ ያልሆነ የልማት ክፍፍል አንዱ ማሳያ ተደርጎ እየተወሰደ ነው።

ነዋሪዎች መንግስት በአስቸኳይ ጣልቃ በመግባት ለባጋደ ድልድይ ሙያዊ ጥናት እንዲያደርግ እና የመንገድና የጤና መሰረተ ልማቶችን እንዲያሟላ ለዎላይታ ታይምስ ( WT Media ) ተናግረዋል።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media