GridArt_20260306_161554584

“ፍትህን በገንዘብ፣ በዝምድናና ስልጣንን መከታ በማድረግ ለማጣመምና ጥፋቶችን ለማስለቀቅ የክልሉ ከፍተኛ የፍትህ ተቋማት አመራሮች ጫና እያደረጉ ነው” ሲሉ በአርባምንጭ ከተማ ውስጥ በሚስቱ የተገደለው ታዋቂው ተጫዋች ቤተሰቦች ቅሬታ ገልጸዋል።

በሟች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የባህር ዳር ከተማ እግር ኳስ ተጫዋች የአለልኝ አዘነ የግድያ መዝገብ ላይ ጥፋተኛ የተባሉ ግለሰቦች ያቀረቡት የይግባኝ ክርክር ከአርባ ምንጭ ወደ ዎላይታ እንዲዛወር መደረጉ፣ “ሆን ተብሎ ፍትህን ለማጓደል የታቀደ ሴራ ነው” ሲሉ የሟች ቤተሰቦቹ ለ WT Media በሰጡት መረጃ ድምፃቸውን አሰምተዋል።

ቤተሰቦቹ ለ WT Media በላኩት የድምፅ ምስክርነትና የሰነድ ማስረጃ፣ የይግባኝ ሂደቱ ከአርባ ምንጭ ምድብ ችሎት ወደ ዎላይታ ምድብ ችሎት እንዲዛወር መደረጉን ፍትህን በገንዘብ፣ በዝምድናና ስልጣንን መከታ በማድረግ ለማጣመም ሴራ ነው በሚል ክፉኛ ተቃውመዋል።

በተለይም ቤተሰቦቹ በድምፅ ፋይሉ ላይ እንዳመለከቱት፣ የችሎቱ መዛወር ከቦታ ርቀት ባለፈ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር የተያያዘ የጥቅም ግጭት እንዳለበት ጠቁመዋል።

በግድያ ወንጀሉ ጥፋተኛ የተባለችው የአደይ ጌታቸው እናት የጎፋ ተወላጅ መሆናቸውን የጠቀሱት ቤተሰቦቹ፣ የወቅቱ የክልሉ ፍርድቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቦጋለ ፈይሳ ጎፋ የቅርብ ዘመድ መሆናቸውን በስጋትነት አንስተዋል።

መዝገቡ ወደ ዎላይታ እንዲዛወር የተደረገው በፕሬዝዳንቱ ትእዛዝ በተሰየሙ ዳኞች አማካኝነት እንደሆነና ይህም “በገንዘብና በትውውቅ” ፍትህን የማጣመም ሂደት መሆኑን ቤተሰቡ በምሬት ገልጸዋል።

የህግ ባለሙያዎችን በማማከር እንደተረዱት፣ የሰበር ችሎት ወይም የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቅርብ ባለ ችሎት ጉዳዩን ማየት ሲችል፣ ሆን ተብሎ ግራ ቀኙ ሳይመክሩበት በሁለት ገጽ ደብዳቤ ብቻ ወደ ዎላይታ መላኩ አግባብ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

መዝገቡ በድብቅና ግራ ቀኙ ሳይመክሩበት በደብዳቤ ብቻ መዛወሩ፣ በሂደቱ ላይ ተገቢ ያልሆነ ተጽዕኖ ሊኖር ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል።

ጉዳዩ ሆን ተብሎ ጥፋተኞችን ለማስመለጥ በዝምድና ወደ ዎላይታ ዞን መዛወሩ ለሟች ቤተሰቦች ፍትህ እንዲዛባ ከማድረግ ባሻገር፣ በነጻነት ተንቀሳቅሶ ፍትህን ለመከታተል እንቅፋት እንደሚሆንባቸው ገልጸዋል።

በደረሰባቸው ሀዘን ላይ ለረጅም ጉዞና ለተጨማሪ እንግልት መዳረጋቸው የሞራልና የገንዘብ አቅማቸውን እየጎዳው መሆኑን ጠቁመዋል።

ቤተሰቡ ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ እና ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቦታ ለውጡን በመቃወም አቤቱታ ቢያስገቡም፣ እስካሁን ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ገልጸዋል።

የተጫዋቹ ቤተሰቦች በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሞራል ስብራት እንደደረሰባቸው ገልጸው፣ ፍርድ ቤቱ ለፊታችን መጋቢት 09 ቀን 2018 ዓ.ም. ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ መያዙ በሂደቱ ላይ ያላቸውን እምነት ይበልጥ እንዳሳጣው ተናግረዋል።

“በመተዋወቅና በአካባቢያዊነት ስራዎች እየተሰሩ ነው” ያሉት ቤተሰቦቹ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ድምፅ እንዲሆናቸው ተማጽነዋል።

ተጫዋች አለልኝ አዘነን በመግደል ወንጀል ተከሰው የነበሩት ባለቤቱ አደይ ጌታቸው እና የእህቷ ባለቤት ሉንጎ ሉቃስ፣ በጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎባቸው ሐምሌ 2017 ዓ.ም. ባዋለው ችሎት በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች አረጋግጫለሁ በማለት፦ በአደይ ጌታቸው ላይ የ16 ዓመት ጽኑ እስራት በሉንጎ ሉቃስ ላይ የ15 ዓመት ጽኑ እስራት መፍረዱ ይታወሳል።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media

#Ethiopia #ደቡብኢትዮጵያ #አርባምንጭ #SouthEthiopia