GridArt_20260306_205658779

ላፉት አምስት ዓመታት የዎላይታ ሕዝብ በታሪክ አይቶት የማያውቀው ዘርፈ-ብዙ ግፍና መከራ ሲፈራረቅበት፣ በፓርላማ “ወከልንህ” ያሉት 13ቱ ተወካዮች ግን ድምፃቸውን አጥፍተው ከርመዋል።

አሁን ምርጫው ጥቂት ወራት ሲቀሩት ግን፣ እነዚህ “የዝምታው ባለቤቶች” ድንገት የሕዝብ ፍቅር ይዟቸው በየቀበሌው ጉብኝት መጀመራቸው በወጣቶችና በምሁራን ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ እየቀሰቀሰ ይገኛል።

ለአብነትም የፌዴራል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ፣ የሁምቦና የአካባቢው ሕዝብ ወኪል ቢሆኑም፣ የሕዝቡን አደራ ወደ ጎን መተዋቸውን WT Media  በተደጋጋሚ ያወጣው ዘገባ ያመለክታል።

ዶከተር ሳሙኤል ቀጥታ የተመረጡበት አበላ አባያ ወረዳ አርሶ አደሮች በገዛ ገንዘባቸው የገዙት ማዳበሪያ ከነጭ አሸዋ ጋር ተቀላቅሎ ሲቀርብላቸውና ወንጀሉ እጅ ከፍንጅ ተይዞ ሳለ፣ ኮሚሽነሩ እርሳቸውን የመረጡ ነዋሪዎች ቀጥታ ያስገቡት ቅሬታ ደብዳቤ እስከ ቢሯቸው ድረስ የተደራጀ ማስረጃ  ቢቀርብላቸውም ሰምተው እንዳልሰሙ ለአመታት ዝምታን መርጠዋል።

ሌላው በአባያ አስፓልት ሥራ ሰበብ በሟቾች ስም የተመዘበረውን በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ብር ጉዳይ የፀረ-ሙስና ኮሚሽነሩ እያወቁት ፍትሕን ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ቢሆኑም፣ በቅርቡ በተቋሙ ላይ የተፈጸመውን ከፍተኛ የሀብት ዘረፋ ለማጋለጥ ቅንጣት ያህል አልተንቀሳቀሱም።

ይልቁንም የሌላ ሕዝብ ተወካዮች (እነ አቶ ክርስቲያን ታደለ እና አቶ አህመድ ሺዴ) ስለ ዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተቆርቁረው እርምጃ እስኪያስወስዱ ድረስ ኮሚሽነሩ የ”ጥቅም ተጋሪነት” በሚመስል ዝምታ ተሸብበው መቆየታቸው የሕዝቡን እምነት ሸርሽሮታል ይላሉ አስተያየት ሰጪዎች።

ከዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ በተጨማሪ ሌሎች ተወካዮች የዎላይታን ሕዝብ ስቃይ ለፓርላማ ከማሳወቅ ይልቅ የግል ጥቅማቸውን መርጠዋል።

የቁጫና የዘይሴ ተወካዮች ለወከላቸው ሕዝብ በፓርላማ ሲሟገቱ፣ የዎላይታ ተወካዮች ግን በስደት የሚሰቃየውን ወጣት፣ የሥራ አጥ ቁጥሩን መጨመርና የአመራሩን ብልሹ አሠራር ከመናገር ይልቅ አንገታቸውን ደፍተው አሳልፈዋል።

አሁን ምርጫው ሲቃረብ እነዚህ ተወካዮች በዎላይታ አካባቢዎች እየዞሩ ጉብኝት መጀመራቸው ለዳግም ምርጫ ሽሚያ እንጂ ለሕዝብ ተቆርቁረው እንዳልሆነ ምሁራንና ወጣቶች ይገልጻሉ።

“አምስት ዓመት ሙሉ የት ነበራችሁ?” የሚለው ጥያቄ በየመድረኩ እየተሰማ ሲሆን፣ ወጣቶች በከፍተኛ ተቃውሞ “በሕዝብ ቁስል ላይ አትቀልዱ” የሚል መልእክት እያስተላለፉ ይገኛሉ።

ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶና ግብረ-አበሮቻቸው፣ ሕዝቡ በታረዘበትና በተራበበት ወቅት የፀረ-ሙስና መዶሻቸውን በሌቦች ላይ ከማሳረፍ ይልቅ ዝምታን መምረጣቸው በታሪክ ተመዝግቧል።

ዛሬ ለምርጫ ካርድ ሲሉ የሚኳትኑት ጉዞ የሕዝቡን ንቀት እንጂ ድጋፍ አያስገኝላቸውም በሚል በርካቶች እየተቹ ነው።

ዎላይታ አሁን የሚፈልገው በሥልጣን የሰከሩ ተወካዮችን ሳይሆን፣ እንደ ቁጫና ዘይሴ ተወካዮች ለሕዝብ ክብርና ጥቅም አንገታቸውን ለሰይፍ የሚሰጡ እውነተኛ ልጆችን ነው በሚል የጠነከረ ሀሳብም ከየአቅጣጫው ከፍ ብሎ እየተደመጠ ይገኛል።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media