1000101679

በዎላይታ ሶዶ ከተማ ማዘጋጃ ቤት እና በፍትህ ተቋማት ውስጥ የተዘረጋው የሙስና መረብ፣ ንጹሐን ዜጎችን ከቀያቸው እያፈናቀለ ለከፍተኛ እንግልት እየዳረገ እንደሚገኝ WT Media በጉዳዩ ዙሪያ የሰራው ምርመራ ዘገባ ያመለክታል።

ለአብነትም አቶ ስምዖን ጫሬ የተባሉ ነባር ነዋሪ፣ ለ41 ዓመታት የኖሩበትንና ግብር የከፈሉበትን ይዞታቸውን በማዘጋጃ ቤት ባለሙያዎች እና በሀሰተኛ ሰነድ አዘጋጆች ተቀናጅቶ በተሰራ ሴራ ተነጥቀው ዛሬ ለስደትና ለኪራይ ቤት ተዳርገዋል።

አቶ ስምዖን ጫሬ በአሮጌ አራዳ ክፍለ ከተማ፣ ኪዳነ ምህረት ቀጠና የሚገኘውን ይዞታቸውን ከመንግስት ተመርተው ያገኙት በ1967 ዓ.ም ነበር።

ለ41 ዓመታት (እስከ 2008 ዓ.ም) ግብር እየከፈሉ በሰላም ሲኖሩበት የቆዩ ቢሆንም፣ በ2006 ዓ.ም “ቦታው ይገባናል” በሚሉ ቤተሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው። ፍርድ ቤት ጉዳዩን አጣርቶ ይዞታው የአቶ ስምዖን መሆኑን በማረጋገጥ በይፋ ውሳኔ ሰጥቶ ነበር።

ጉዳዩ በይግባኝ ሂደት ላይ እያለ፣ ወ/ሮ አለምቱ ጫሬ የተባሉ ግለሰብ ከማዘጋጃ ቤት ባለሙያዎች ጋር በመመሳጠር አቶ ስምዖን በግፍ እንዲታሰሩ አደረጉ።

አቶ ስምዖን በማረሚያ ቤት በነበሩበት ወቅት ማዘጋጃ ቤቱ የአቶ ስምዖንን የ80 ቅጠል ቆርቆሮ መኖሪያ ቤት “በሀራጅ” አውጥቶ በመሸጥ ቤቱ እንዲፈርስ አደረገ።

ይዞታውም ለብራይት ሀውስ ሆቴል ባለቤት ለአቶ ተወድሮስ ሙላቱ ተሸጠ።

ይሁን እንጂ፣ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በአካል ተገኝቶ የአካባቢውን ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች በመስማት፣ ይዞታው የአቶ ስምዖን መሆኑን በድጋሚ በማፅናት መሬቱ ለባለቤቱ እንዲመለስ ወሰነ።

አቶ ተወድሮስ ሙላቱ በፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት መሬቱን ለአቶ ስምዖን አስረክቦ ቢወጣም፣ የማዘጋጃ ቤት አመራሮች ግን ከሚመጣባቸው ተጠያቂነት ለማምለጥ አዲስ ሴራ ጠነሰሱ።

አቶ ስምዖን ከእስር ወጥተው ወደ ይዞታቸው እንዳይመለሱ በማድረግ በማዘጋጃ ቤቱ በኩል ያለምንም ህጋዊ ሰነድ ወ/ሮ አለምቱ ጫሬ ለሦስተኛ ወገን (ለአቶ ግሩም አለማየሁ) እንድትሸጥ ሁኔታዎች ተመቻቹላት።

የሚገርመው ድርጊት ማዘጋጃ ቤቱ በአቶ ስምዖን ጫሬ ሳይት ፕላን ላይ ሌላ ሳይት ፕላን ሰርቶ ለአቶ ግሩም አለማየሁ በመስጠት ይዞታው እንዲተላለፍ ማድረጉ ነው።

አቶ ስምዖን በእጃቸው ህጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ፣ የግብር ካርኒ እና የሶስት ደረጃ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ቢኖራቸውም፣ በማዘጋጃ ቤትና በፍትህ ተቋማት ባሉ ደላላ አመራሮች ምክንያት ወደ ይዞታቸው መመለስ አልቻሉም።

ዛሬ አቶ ስምዖን ልጆቻቸውን ይዘው በሰው ቤት ተከራይተው ሲኖሩ፣ ንብረታቸውን የዘረፉና ቤታቸውን ያፈረሱ ግለሰቦች ግን በማን አለብኝነት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

ይህ በአቶ ስምዖን ጫሬ ላይ የደረሰው በደል የዎላይታ ሶዶ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምን ያህል በሙስና እንደተዘፈቀ የሚያሳይ ህያው ማስረጃ ነው። ሳይት ፕላን እየደራረቡ መስጠት እና የፍርድ ቤት ውሳኔን አጣሞ መፈጸም የወንጀል ቁንጮ ነው።

የከተማው አስተዳደር እና የክልሉ ፍትህ ቢሮ ይህንን የተደራጀ ዘረፋ በአስቸኳይ እንዲመረምሩ እና የአቶ ስምዖን ይዞታ እንዲመለስ WT Media ጥሪውን ያቀርባል።

🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏

Voice of Marginalized Community – WT Media