የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት በምሥራቅ ጉራጌ ዞን ምሥራቅ መስቃን ወረዳ የሲቪል ነዋሪዎችን ደህንነት እንዲጠበቅ ሲል ጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትህ ፓርቲ ጠይቀዋል።
ፓርቲው የሲቪል ነዋሪዎችን ደህንነት እንዲያስጠበቅ ሲል የጠየቀው ትናንት ባወጣው መግለጫ ነው፡፡ ፓርቲው በዚሁ መግለጫው በምሥራቅ መስቃን ወረዳ በንጹሃን ዜጎች ላይ በተደጋጋሚ በታጣቂዎች ይፈጸማል ያለው ጥቃት እንዳሳሰበው ገልጿል፡፡
በወረዳው ከታህሳስ 16 እስከ የካቲት 26 2018 ዓም ድረስ ባለው ሁለት ወራት ውስጥ በታጣቂዎች በግፍ ተገድለዋል ያላቸውን የ16 ሰዎችን የሥም ዝርዝር፣ ዕድሜና የህይወት ታሪካቸውን ከመግለጫው ጋር በአባሪነት አያይዟል።
ጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትህ ፓርቲ መግለጫውን መውጣት ያስፈለገው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እና ምሥራቅ ጉራጌ ዞን መስተዳድር ህዝቡን ከተደጋጋሚ የታጣቂዎች ጥቃት መከላከል ባለመቻላቸው መሆኑን የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጀሚል ሳኒ ገልጸዋል።
በአካባቢው የተሰማሩት የፀጥታ ሀይሎች ህዝቡ ራሱን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት ሳይቀር እያስተጓጎሉ ሥለመሆናቸው ፓርቲው ባሰባሰበው መረጃ ማረጋገጡን አቶ ጀሚል ተናግረዋል።
የክልሉና ምሥራቅ ጉራጌ ዞን መስተዳድሮች የጥቃት በሮችን የመከላከል ሥራ እንዲሠሩና የህዝቡን ደህንነት የማስጠበቅ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ በመግለጫው መጠየቁን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው ተናግረዋል።
ኃላፊው አክለውም“ አካባቢውን በሚያምሱ ታጣቂዎች ቡድኖች ላይ የማያዳግም ህግ የማስከበር እርምጃ እንዲወሰድ፣ እንዲሁም ይህን ሃላፊነት ባልተወጡና ህዝብን ለጥቃት እያጋለጡ ባሉ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ላይ ህጋዊ ተጠያቂነት እንዲሰፍን እንፈልጋለን“ ብለዋል።