በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጋሞ ዞን ሦስት ወረዳዎች በተከሰተው አሰቃቂ የመሬት ናዳ አደጋ እስካሁን የተገኘው የአስከሬን ብዛት 48 መድረሱን የጋሞ ዞን ፖሊስ አስታውቋል።
አደጋው ከሰዓት ወደ ሰዓት እየተባባሰ የመጣ ሲሆን፣ አሁንም በጭቃና በናዳ ተቀብረው ያልወጡ በርካታ ዜጎች እንዳሉ ተገልጿል።
እንደ ዞኑ ፖሊስ መረጃ፣ በጋጮ ባባ፣ በቦንኬ እና በላካ ወረዳዎች በደረሰው አደጋ እስካሁን የ48 ዜጎች አስከሬን ተገኝቷል።



በተለይም አስከሬን ፍለጋ የወጡ ሰዎች ላይ በድጋሚ ናዳ መከሰቱ ለሟቾች ቁጥር መጨመር ዋናው ምክንያት ሆኗል።
በሦስቱ ወረዳዎች እስካሁን ድረስ የ95 ሰዎች ደብዛ ጠፍቶ ይገኛል። እነዚህ ዜጎች በናዳው ተወስደው ወይም በጭቃ ተቀብረው ሊሆን እንደሚችል በመገመቱ፣ ቤተሰቦቻቸው በከፍተኛ ጭንቀትና ሐዘን ላይ ይገኛሉ።
የነፍስ አድን ሥራው በዞኑ ፖሊስ፣ በአካባቢው አስተዳደርና በማኅበረሰቡ ትብብር ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ሆኖም ግን ፍለጋው በአብዛኛው በሰው ኃይልና በቀላል መሣሪያዎች እየተከናወነ መሆኑ ሥራውን አዝጋሚ አድርጎታል።
አሁንም አካባቢው ለተጨማሪ ናዳ ተጋላጭ በመሆኑ የነፍስ አድን ሠራተኞቹን ሕይወት ስጋት ላይ ጥሏል።
ይህ በጋሞ ምድር የደረሰው እልቂት አገራዊ ትኩረትን የሚሻ ትልቅ ሰብአዊ ቀውስ ነው።
የፌዴራል መንግሥትና ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች በአፋጣኝ የነፍስ አድን መሣሪያዎችንና የሕክምና ቁሳቁሶችን ወደ ስፍራው እንዲልኩ WT Media ጥሪውን ያቀርባል።
WT Media ይህ በጋሞ ምድር የደረሰው እልቂት አገራዊ ትኩረትን የሚሻ ትልቅ ሰብአዊ ቀውስ መሆኑን በመገንዘብ፣ ትናንት አደጋው ከተከሰተበት የመጀመሪያው ሰዓት ጀምሮ መረጃዎችን በቅርበት በመከታተል ለሕዝብ ሲያደርስ መቆየቱ ይታወሳል።
ሚዲያችን አሁንም በስፍራው ካሉ ምንጮች ጋር በመገናኘት ወቅታዊ መረጃዎችን ለናንተ ማድረሱን ይቀጥላል።
ለተጎዱ ቤተሰቦችና ለሟች ወገኖቻችን በድጋሚ መጽናናትን እንመኛለን።