በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ የሟቾች ቁጥር ከ107 በላይ መድረሱና በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸው መላውን አገር በሐዘን ሰብሮታል።
ሆኖም ይህ ሰብአዊ ቀውስ ለተጎጂዎች የልብ ስብራት ሲሆን፣ በሙስና ለተጨማለቁ የክልሉ ካድሬዎች ግን “ሌላ ሲሳይ” ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት በምሁራንና በማኅበረሰብ አንቂዎች ዘንድ በስፋት እየተሰነዘረ ይገኛል።


WT Media ከዚህ ቀደም በጎፋ ዞን (ኬንቾ ሻቻ) በደረሰው አደጋ የተሰበሰበውን ወደ አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የእርዳታ ገንዘብ ምዝበራና እስካሁን ምንም የህግ ተጠያቂነት ያልተሰጠበትን በሰፊው በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።
ዛሬ ላይ የጋሞ ዞን አደጋ ሲከሰት፣ ያ የታሪካዊ ስርቆት ትዝታ በብዙዎች አእምሮ ውስጥ ድቅን ብሏል።
በጎፋው አደጋ ወቅት ከተሰበሰበው በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ውስጥ ለተጎጂዎች ቤት ለመሥራት ኃላፊነት የወሰደው የጥላሁን ከበደ መዋቅር፣ መሠረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎትን ያላሟሉ ሽንት ቤት የሌላቸውና ለቤት ጣሪያ የማይሆኑ ቆርቆሮዎች የተመቱባቸውን ቤቶች ጥቂት አባወራዎች ላይ በመጫን ቀሪውን ገንዘብ ለካድሬዎች ቀለብ ማድረጉ ተጋልጧል።
እንደ ቀይ መስቀልና Habitat ያሉ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች በግልጽና በጥራት ቤቶችን ሠርተው ሲያስረክቡ፣ የመንግሥት መዋቅር ግን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ሲያጭበረብር እጅ ከፍንጅ ተይዟል።
ምሁራን እንደሚጠቁሙት፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ ነባርና አዳዲስ ካድሬዎች አብዛኞቹ “እንደ ኮዳ ውኃ የተቀዱበትን ዕቃ ቅርጽ የሚይዙ” እንጂ ለሕዝብ ጥቅም የሚቆረቆር ሕሊና የላቸውም።
በጋሞ ዞንም አደጋው እንደደረሰ፣ ልምድ ያላቸው “የቀን ጅቦች” እርዳታውን ለመቀራመት አሰፍስፈው መጠበቃቸው አልቀረም።
በጋሞ ዞን የጋራ ላይ ተንጠልጥለው የሚኖሩ ድሆች በናዳ ሲቀበሩ፣ አመራሩ ግን በቆላማ አካባቢዎች (በዘይሴዎች ላይ) የፖለቲካ ሴራ በመሸረብና እሳት በመለኮስ ሲጠመድ ከርሟል።
አሁን የተከሰተው አደጋ ለእነዚህ ካድሬዎች “ገቢ ማሰባሰቢያና የዝርፊያ ርዕስ” እንዳይሆን ትልቅ ቅድመ-ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
ምሁራን የመፍትሔ ምክረ-ሐሳቦች ሲገልፁ፦ የጋሞ ዞን የጎፋውን የውርደት መንገድ እንዳይከተል፣ ድህረ-ቀውሱ (Post-disaster management) በከፍተኛ ጥንቃቄ መመራት እንዳለበት ይጠቁማሉ።
የእርዳታ ገንዘቡን የሚያስተባብረው ኮሚቴ በመንግሥት ሰዎች ብቻ የተሞላ ሳይሆን፤ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከታዋቂ ምሁራን፣ ከቀይ መስቀል እና ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች (በተለይ ከጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ) የተውጣጣ መሆን አለበት ይላሉ።
የማይስማሙ ሰዎች በአንድ ኮሚቴ መኖራቸው ምዝበራን ይቀንሳል በሚልም ምሁራን ያብራራሉ።
ለተጎጂዎች የሚሰበሰበው ገንዘብ በገለልተኛ ኦዲተር በየጊዜው እንዲመረመርና ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ ግፊት መደረግ እንዳለበትም አሳስበዋል።


ባለሥልጣናት “አልቃሽ መስለው” ፎቶ ከመነሳት ወጥተው፣ ለናዳ ተጋላጭ የሆኑ ወገኖችን ወደ ሜዳማ ስፍራዎች በቋሚነት የሚያሰፍሩበትን ስትራቴጂ ሊነድፉ ይገባል በሚልም ጠቁመዋል።
“በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመሬት መንሸራተት እንደ ዓመት በዓል በየዓመቱ እየተደጋገመ ድሃውን እየቀበረ ይገኛል። ይህ መቅሰፍት ሳይሆን የአመራር ውድቀት ውጤት ነው። ለጋሞው አደጋ ገንዘብ የምታዋጡ ዜጎች፣ ገንዘባችሁ ለካድሬ መጫወቻ እንዳይሆን አካውንቱ በመንግሥትና በገለልተኛ ወገኖች በጋራ መከፈቱን ማረጋገጥ” እንዳለበትም አሳስበዋል።
በድጋሚ የሞቱትን ነፍስ ይማር፤ የተረፉትን ግን ከቀን ጅቦች ዝርፊያ እንታደጋቸው መልዕክታችን ይሆናል!
🎙️ ማሳሰቢያ፦ WT Media በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ትኩረት ያላገኙ ለተጨቆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጥ ሲሆን እውነትን፣ ሀቅንና ፍትሕን መሠረት በማድረግ፣ የመረጃ ሰጪዎችን ምስጢርና ደኅንነት በመጠበቅ በሌሎች ሚዲያዎች የማይሰሙ የጭቁኖች ድምፅ ዘውትር እዚሁ ይሰማልና ስለአብሮነታችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው! የእናንተው የጭቁኖች አገልጋይ ነን🙏
Voice of Marginalized Community – WT Media
በጎፋው አደጋ ወደ አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የእርዳታ ገንዘብ ያጭበረበሩ ከፍተኛ አመራሮች ሳይጠየቁ በጋሞው እልቂትም ይደግሙ ይ