በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጋሞ ዞን የደረሰው አሰቃቂ የመሬት ናዳ አደጋ ከ107 በላይ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈው ድንገት ሳይሆን፣ በአካባቢው ተደጋጋሚ የአፈር መሸርሸርና የናዳ ምልክቶች እየታዩ መሆኑ እየተነገረ ነው።


በዚህ ሂደት ውስጥ ዋነኛው ተጠያቂ የሚሆነው ደግሞ በአደጋው ቀጠና ስር የሚገኘውና በውኃና በጂኦሎጂ (Geology) ሳይንስ ዘርፍ ትልቅ ስም ያለው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ነው።
ዩኒቨርሲቲው አደጋው ከተከሰተ በኋላ ዛሬ“ተመራማሪዎችን ወደ ስፍራው ላኩ” የሚለው መግለጫ አሳማኝ ያልሆነባቸውና የአመራር ክፍተቱን የሚያሳዩ ነጥቦች መታየቱን አንድ ምሁር እንደሚከተለው ለ WT Media ተናግረዋል።
አንድ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢው ማኅበረሰብ ችግር ፈቺ ነው የሚባለው አደጋው ከደረሰ በኋላ ለቅሶ በመድረስ ሳይሆን፣ አስቀድሞ ሳይንሳዊ ግምቶችን (Early Warning Systems) በማቅረብ ነው።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ በቂ ምሁራን እያሉት ለምን የጋሞ ተራራማ አካባቢዎችን የናዳ ስጋት አስቀድሞ አላጠናም?
ለምን ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ቀበሌዎችን ለይቶ ለመንግሥትና ለማኅበረሰቡ ማስጠንቀቂያ አልሰጠም? የዩኒቨርሲቲው የምርምር በጀት ለምን ለቅድመ-ጥናት ሳይሆን ለድህረ-አደጋ የፎቶ ሪፖርት ውይይት ይውላል? የሚሉ ከባድ ጥያቄዎች ይነሳሉ።
ዩኒቨርሲቲው አሁን የላከው ቡድን “ምክረ-ሐሳብ ያቀርባል” ማለቱ ዘግይቷል። ሳይንሳዊ እውቀት ዋጋ የሚኖረው ዜጎች በሕይወት እያሉ ከቀያቸው እንዲነሱ ማድረግ ሲችል ብቻ ነው።
የ107 ሰዎች ሕይወት ካለፈ በኋላ የሚቀርብ ጥናት ለሞቱት ወገኖች ትርጉም የለውም።
ይህ የሚያሳየው ዩኒቨርሲቲው ከማኅበረሰቡ የዕለት ተዕለት ስጋት ተለይቶ በዝግ ግቢ ውስጥ ብቻ እንደሚሠራ ነው ምሁራን ይገልፃሉ።
የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር አደጋው በደረሰ በአምስተኛው ቀን “ነገ ሄጄ ሐዘን እገልጻለሁ” ማለቱ ተቋሙ ምን ያህል ከአካባቢው እውነታ እንደራቀ ማሳያ ነው።
ዩኒቨርሲቲው በአደጋው ማግስት ሳይንሳዊ መረጃዎችን በመያዝ የነፍስ አድን ሥራውን በቴክኖሎጂ (ለምሳሌ ድሮን ወይም የአፈር መመርመሪያ) ማገዝ ሲገባው፣ ቀናት በውይይት ማሳለፉ የአመራር ብቃት ማነስን ያሳያል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በክልሉ የሚከሰቱ ተደጋጋሚ አደጋዎችን አስቀድሞ የማጥናትና የመከላከል ሞራልና ሙያዊ ኃላፊነት ነበረበት።
አሁን ከደረሰው እልቂት በኋላ የሚሰጡ መግለጫዎች የተቋሙን ዝና ከመገንባት ባለፈ ለተጎጂው ሕዝብ የሚፈይዱት ነገር አነስተኛ ነው።
ተቋሙ ከዚህ ስህተቱ ተምሮ፣ በቀሪዎቹ ተጋላጭ አካባቢዎች ላይ አሁኑኑ ሳይንሳዊ ግፊት በማድረግ ሕዝቡን የማስነሳት ሥራ እንዲሠራ እናሳስባለን።