በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኦቶና ሆስፒታል መውደም ዝምታ የታከለበት እልቂት በመፍጠሩ በጥቂት ወራት ውስጥ ከአንድ ሺህ በላይ ዜጎች ሕይወት ማጣታቸውን አንድ የዳሰሳ ጥናት አመልክቷል።
የሚሊዮኖች የጤና መጠጊያ የነበረው በዎላይታ ሶዶ የሚገኘው የኦቶና ሆስፒታል በእሳት አደጋ መውደሙን ተከትሎ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እጅግ አሰቃቂ የሆነ ብሔራዊ አደጋ እየተከሰተ መሆኑን WT Media የዘርፉን ባለሙያዎችን በመጠቀም ያደረገው የዳሰሳ ጥናት ውጤት ያመለክታሉ።
ሆስፒታሉ አገልግሎት ማቋረጡን ተከትሎ፣ ታክመው መዳን ይችሉ የነበሩ ከ1 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ሕይወታቸው ማለፉ ተገምቷል።

የጤና መድህን (CBHI) ተጠቃሚ የሆኑና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ብቸኛ አማራጫቸው የነበረው ኦቶና ሆስፒታል ነበር።
ሆስፒታሉ ከወደመ ወዲህ ወደ ግል ሕክምና ተቋማት ሄደው ለመታከም አቅም የሌላቸው አርሶ አደሮች ቤታቸው ቁጭ ብለው ለሞት እየተዳረጉ ይገኛሉ።
ታክመው መዳን የሚችሉ ቀላል ሕመሞች ሳይቀር፣ የሪፈራል ሥርዓቱ በመናጋቱ ምክንያት ወደ ከፋ ደረጃ ተቀይረው የዜጎችን ሕይወት እየቀጠፉ ነው።
እንደ ዳሰሳ ጥናት፣ ሆስፒታሉ ከወደመበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በየቤቱና በየቀበሌው የሞቱ ዜጎች ቁጥር ከ1 ሺህ በላይ እንደሚሆን ይገመታል።
ይህ እልቂት በይፋ ባይመዘገብም፣ የማኅበረሰቡን የጤና ዋስትና ክፉኛ የናጋና ዝምታ የታከለበት ብሔራዊ አደጋ ሆኗል።
ሆስፒታሉ በወደመ ማግስት ከተለያዩ ወገኖች ከፍተኛ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ መሰብሰቡ ቢነገርም፣ የተሰበሰበው ሀብት በግልጽ አለመታወቁና መልሶ ግንባታው በታሰበው ፍጥነት አለመጀመሩ በሕዝቡ ዘንድ ትልቅ ጥርጣሬና ቅሬታ ፈጥሯል።
የክልሉ መንግሥት ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆን፣ ለሚሊዮኖች ሕይወት ግድየለሽ የመሆኑ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
የኦቶና ሆስፒታል መውደም የአንድ ተቋም መጥፋት ብቻ ሳይሆን፣ የሚሊዮኖች የሕይወት ዋስትና መቃጠል ነው።
የፌዴራል መንግሥትና የጤና ሚኒስቴር ጉዳዩን እንደ ብሔራዊ አደጋ በመቁጠር አስቸኳይ ጣልቃ ገብነት እንዲያደርጉ እያሳሰብን የሰው ሕይወት በፖለቲካዊ ቸልተኝነትና በምዝበራ ስጋት ሊቀጠፍ አይገባም እንላለን!
ማሳሰቢያ፦ ይህ የምርመራ ዘገባ WT Media የዘርፉን ባለሙያዎች በማሳተፍና መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በዳሰሳ ጥናት በመፈተሽ ያጠናቀረው መረጃ ነው።