GridArt_20260314_161010245

የዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጉብኝት በደቡብ ክልል አመራሮች ላይ ከፍተኛ ፍርሃት የፈጠረው ለምን እንደሆነ ያውቃሉ ? ለጎፋ ወገኖች የተሰበሰበው እርዳታ ገንዘብ የት ገባ ?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ የተከሰተውን የመሬት ናዳ አደጋ ተከትሎ በስፍራው በተገኙበት ወቅት በክልሉ አመራሮች ላይ እጅግ የበረታ ቁጣ መግለጻቸውን ለ WT Media የደረሱ ታማኝ ምንጮች አጋልጧል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የክልሉን አመራሮች “ሌቦች” በሚል መጥራታቸውን ተከትሎ በአሁኑ ሰዓት በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ዘንድ ታላቅ መደናገጥና ፍርሃት ሰፍኖ ይገኛል።

ከዚህ ቀደም በጎፋ ዞን የመሬት መንሸራተት አደጋ በደረሰ ወቅት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት አገራዊ ጥሪ መሠረት ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት ወደ አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ተሰብስቦ ነበር።

ሆኖም ይህ ግዙፍ የገንዘብ መጠን በአመራሮቹ እጅ ከገባ በኋላ ለታለመለት ዓላማ ሳይውል መመዝበሩንና እስካሁንም ተጠያቂነት አለመስፈኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እጅግ እንዳስቆጣ ተጠቁሟል።

ከዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ጉብኝታቸው መልስ በቀጥታ አደጋው ወደደረሰበት የጋሞ ዞን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በክልሉ በአመራር ደረጃ የሚፈጸመው ሙስና እና ብልሹ አሠራር የአደባባይ ምስጢር መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ምንጩ ገለጻ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁኔታው እጅግ ማዘናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በቅርቡ በአመራሩ ላይ ጠንካራ ፖለቲካዊና ሕጋዊ እርምጃ ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ አንድ ከፍተኛ አመራር ለ WT Media እንደገለጸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሉ ሌቦች ላይ የማያዳግም እርምጃ ከወሰዱ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ትልቅ አክብሮትና ድጋፍ ያገኛሉ።

“ሕዝቡ የራሱን አመራሮች በሙስና መጥገብ ተማርሯል፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እርምጃ የሕግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ ከሆነ ትልቅ ለውጥ ይመጣል” ሲል አመራሩ አክሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) አደጋው በደረሰበት ወቅት ሀገር ውስጥ ባይሆኑም፣ ዛሬ መጋቢት 05/2018 ዓ.ም ወደ ስፍራው በመገኘት ተጎጂዎችን ማጽናናታቸው በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን አትርፎላቸዋል።

ሆኖም ይህ ጉብኝታቸው ከለቅሶ መድረስ ባለፈ፣ በክልሉ ያለውን ሥር የሰደደ የሙስና መዋቅር ለማጽዳት መነሻ እንደሚሆን ይጠበቃል።