GridArt_20260319_164505010

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በታጣቂዎች በተከፈተ ድንገተኛ ተኩስ ቆስለው በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ሲታከሙ የነበሩት የክልሉ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አዱኛ አዛዥ፣ ዛሬ መጋቢት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 6:00 ሰዓት አካባቢ ሕይወታቸው ማለፉን WT Media አረጋግጧል።

ወ/ሮ አዱኛ አዛዥ ትላንት መጋቢት 09 ቀን 2018 ዓ.ም ወደ አርባ ምንጭ ከተማ በመጓዝ ላይ እያሉ፣ በጋርዱላ ዞን ሆልቴና ሽላሌ አካባቢ በታጠቁ ኃይሎች ድንገተኛ ተኩስ ተከፍቶባቸዋል።

በጥቃቱ ክፉኛ ተመትተው ወደ አርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን፣ ትላንት ረጅም ሰዓታት የፈጀ ቀዶ ጥገና ቢደረግላቸውም ሕይወታቸውን ማዳን አልተቻለም።

በጥቃቱ የቆሰሉ ሌሎች ተጓዦችም በአሁኑ ወቅት በሕክምና ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

ከአርባ ምንጭ እስከ ጋቶ ያለው የፌዴራል መንገድ፣ በተለይም በጋርዱላ ዞን የሚያልፈው ክፍል፣ የታጠቁ ኃይሎች ተሽከርካሪዎችን የሚያስቆሙበት፣ ዘረፋ የሚፈጽሙበትና በሰላማዊ ዜጎች ላይ ተኩስ በመክፈት የሚገድሉበትና አካል የሚያጉድሉበት ቀጠና ሆኗል ሲል አንድ ከትናንቱ አደጋ የተረፈ ግለሰብ ለ WT Media አስረድተዋል።

ትላንት ብቻ በጠራራ ፀሐይ በበርካታ ተሽከርካሪዎች ላይ ተመሳሳይ ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን፣ ብዙዎች በፈጣሪ እርዳታ በጥቅቱ ከማምለጣቸው ባለፈ የክልሉ ከፍተኛ አመራር ሕይወት አልፏል።

ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በአካባቢው በተፈጸሙ ጥቃቶች ላይ በተሳተፉ ወንጀለኞች ላይ በክልል መንግሥት ተገቢ እርምጃ አለመወሰዱ፣ እንዲያውም የተያዙ ወንጀለኞች በጥቅም ትስስር ወዲያው ነፃ ተብለው እንዲለቀቁ መደረጉ፣ ወንጀለኞቹ ይበልጥ እንዲደፍሩና ጥቃታቸውን እንዲያባብሱ አድርጓቸዋል።

ይህ ሁኔታ ሳይቆም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ችግሩን ቸል ማለቱ፣ የሕዝብ ሕይወትና ንብረት በከፍተኛ አደጋ ላይ እንዲወድቅ አድርጓል።

አሁንም ከአርባ ምንጭ ከተማ ወደ ኮንሶ የሚወስደው ወሳኝ የንግድ መስመር ከፍተኛ የፀጥታ ችግር አለበት።

መንግሥት የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ቀዳሚ ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎችን በአስቸኳይ እንዲቆጣጠር የአከባቢው ነዋሪዎች እያሳሰቡ ይገኛሉ።

WT Media የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ በቅርበት መከታተሉን ይቀጥላል።